ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 17:15-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤ እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤ እግዚአብሔር እንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።

16. አምላካቸው እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ አልፈጸሙም፤ አቅልጠውም ሁለት የጥጃ ምስልና የአሼራን ምስል ዐምድ ሠሩ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰገዱ፤ በኣልን አመለኩ፤

17. እንዲሁም ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ጥንቈላና መተት አደረጉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ፤ ለቊጣም አነሣሡት።

18. ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ የይሁዳ ነገድ ብቻ ሲቀር እስራኤልን ከፊቱ አራቀ።

19. ይሁዳም ቢሆን ከእስራኤል የተቀበለውን ልማድ ተከተለ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም።

20. ስለዚህ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ ተዋቸው፤ አስጨነቃቸው፤ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸውም ድረስ በማራኪዎቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።

21. እስራኤልን ከዳዊት ቤት ከለየ በኋላ፣ እነርሱ የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እስራኤል እግዚአብሔርን እንዳይከተል በማሳት ትልቅ ኀጢአት እንዲሠራ አደረገ።

22. እስራኤላውያንም በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ጸኑ፤ ከዚያም አልተመለሱም።

23. እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት ሁሉ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በዚያው ቀጠሉበት፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ከሀገሩ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ፤ አሁንም በዚያው ይገኛል።

24. የአሦርም ንጉሥ ሕዝቡን ከባቢሎን፣ ከኩታ፣ ከአዋና ከሐማት፣ ከሴፈርዋይም ከተሞች አምጥቶ በእስራኤላውያን ቦታ እንዲገቡ በሰማርያ ከተሞች አሰፈራቸው፤ እነርሱም ሰማርያን ወርሰው በከተሞቿ ይኖሩ ጀመር።

25. በዚያ መኖር እንደ ጀመሩም እግዚአብሔርን አላመለኩም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አንበሶች ሰደደባቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹን ሰብረው ገደሉ።

26. ለአሦርም ንጉሥ፣ “ወደ ሰማርያ ከተሞች ወስደህ ያሰፈርኸው ሕዝብ የዚያ አገር አምላክ የሚፈልገውን አላወቀም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰብሮ የሚገድል አንበሳ ላከበት” የሚል ወሬ ደረሰው።

27. ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ “ከሰማርያ ማርካችሁ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን፣ በእዚያው እንዲኖር መልሳችሁ ውሰዱትና የአገሩ አምላክ ምን እንደሚፈልግ ሕዝቡን ያስተምር” ሲል አዘዘ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 17