ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 17:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዘጠኝ ዓመትም ገዛ።

2. እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ክፉ ሥራው ግን ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩት የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙትን ያህል አልነበረም።

3. የአሦር ንጉሥ ሰልም ናሶር ሊወጋው መጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ገበረለትም።

4. የአሦር ንጉሥ ግን ሆሴዕ እንደ ከዳው ተገነዘበ፤ ምክንያቱም ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሲጎር መልክተኞች ስለላከና በያመቱም ያደርግ እንደ ነበረው ለአሦር ንጉሥ ስላልገበረ ነው፤ ከዚህም የተነሣ ስልምናሶር ይዞ ወህኒ ቤት አስገባው።

5. የአሦርም ንጉሥ አገሩን በሙሉ ወረረ፤ ወደ ሰማርያም ገሥግሦ ሦስት ዓመት ከበባት።

6. በሆሴዕ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም በምርኮ ወደ አሦር አፈለሳቸው። እነዚህም በአላሔ፣ ጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብ እንዲሁም በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ።

7. እንግዲህ እስራኤላውያን ይህ ሁሉ ሊደርስባቸው የቻለው፣ ከግብፅ ምድር ከፈርዖን አገዛዝ ከግብፅ ንጉሥ ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ስለ በደሉት ነው፤ እንዲሁም ሌሎች አማልክትን በማምለክ፣

8. እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳዶ ያወጣቸውን የአሕዛብንና የእስራኤልም ነገሥታት ወደ ምድሪቱ ያገቡትን አጸያፊ ልማድ ስለ ተከተሉ ነበር።

9. እስራኤላውያን በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ትክክል ያልሆነ ነገር በስውር አደረጉ፤ ከቃፊር መጠባበቂያ ማማ አንሥቶ እስከ ተመሸገው ከተማ ባሉት መኖሪያዎቻቸው ሁሉ በሚገኙት ኰረብቶች ላይ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ።

10. በእያንዳንዱ ኰረብታ ላይና በእያንዳንዱም የተንሰራፋ ዛፍ ሥር ዐምደ ጣዖትና የአሼራን ምስል ዐምዶች አቆሙ።

11. እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳዶ ያስወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉትም ሁሉ፣ በየኰረብታው ላይ ዕጣን አጤሱ፤ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጣ ክፉ ነገር አደረጉ።

12. እግዚአብሔር፣ “ይህን ማድረግ አይገባችሁም” ቢላቸውም እንኳ እነርሱ ጣዖታትን አመለኩ።

13. ይህም ሆኖ እግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለ ራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።

14. ይሁን እንጂ እነዚህም አልሰሙም፤ እግዚአብሔር አምላካቸውን እንዳልታመኑበት እንደ አባቶቻቸው ዐንገታቸውን አደነደኑ።

15. ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤ እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤ እግዚአብሔር እንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።

16. አምላካቸው እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ አልፈጸሙም፤ አቅልጠውም ሁለት የጥጃ ምስልና የአሼራን ምስል ዐምድ ሠሩ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰገዱ፤ በኣልን አመለኩ፤

17. እንዲሁም ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ጥንቈላና መተት አደረጉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ፤ ለቊጣም አነሣሡት።

18. ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ የይሁዳ ነገድ ብቻ ሲቀር እስራኤልን ከፊቱ አራቀ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 17