ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 15:9-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

10. የያቤስ ልጅ ሰሎም በዘካርያስ ላይ አሤረበት፤ በሕዝቡ ፊት አደጋ ጥሎ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

11. በዘካርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦአል።

12. በዚህም እግዚአብሔር ለኢዩ፣ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” ሲል የተናገረው ቃል ተፈጸመ።

13. የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም በእስራኤል ላይ ነገሠ። በሰማርያ ተቀምጦ አንድ ወር ገዛ።

14. የጋዲ ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ በመሄድ አደጋ ጥሎ የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን ገደለው፤ ከዚያም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

15. በሰሎም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራና የጠነሰሰውም ሤራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

16. በዚያን ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ በቲፍሳና በከተማዪቱ ነዋሪዎች ላይ ሁሉ፣ በአካባቢዋም ጭምር አደጋ ጣለ፤ ይህን ያደረገውም የከተማዪቱን በሮች ለመክፈት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ነበር፤ ቲፍሳን መታት፤ የነፍሰጡሮችንም ሆድ ሁሉ ቀደደ።

17. የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት፣ የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያ ተቀም ጦም ዐሥር ዓመት ገዛ።

18. በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ በዘመኑም ሁሉ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

19. ከዚያም የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌ ልሶርፀ ምድሪቱን ወረረ፤ ምናሔም ርዳታውን ለማግኘትና በመንግሥቱ ላይ ያለውን ይዞታ ለማጽናት ሲል፣ አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው።

20. ምናሔም ገንዘቡ እንዲዋጣ ያደረገው ከእስራኤል ሲሆን፣ ይህንንም ያደረገው ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ እያንዳንዱ ሀብታም አምሳ፣ አምሳ ሰቅል ብር እንዲያዋጣ በማስገደድ ነበር። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ በዚያች አገር አልቈየም፤ ተመልሶ ሄደ።

21. በምናሔም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 15