ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 15:30-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. ከዚያም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ አሤረበት፤ አደጋ ጥሎም ገደለው፤ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በነገሠ በሃያኛው ዓመትም ሆሴዕ በፋቁሔ እግር ተተክቶ ነገሠ።

31. በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸማቸውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

32. የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ።

33. ሲነግሥም ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ ኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ስትሆን፤ ኢየሩሳ ትባል ነበር።

34. አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

35. ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። ኢዮአታም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የላይኛውን በር መልሶ ሠራ።

36. በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

37. በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔን ይሁዳን እንዲወጉ አደረገ።

38. ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ አባቶቹ በተቀበሩበትም፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 15