ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 15:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ሲነግሥም ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።

3. አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ ዓዛርያስም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

4. ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና እጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።

5. እግዚአብሔርም ንጉሡን እስከሚሞትበት ቀን ድረስ በለምጽ መታው፤ በተለየ ቤትም ይኖር ነበር። በዚያን ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር።

6. በዓዛርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

7. ዓዛርያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ በአባቶቹ መቃብር አጠገብ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአታምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

8. የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ስድስት ወርም ገዛ።

9. አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

10. የያቤስ ልጅ ሰሎም በዘካርያስ ላይ አሤረበት፤ በሕዝቡ ፊት አደጋ ጥሎ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

11. በዘካርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦአል።

12. በዚህም እግዚአብሔር ለኢዩ፣ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” ሲል የተናገረው ቃል ተፈጸመ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 15