ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 15:19-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ከዚያም የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌ ልሶርፀ ምድሪቱን ወረረ፤ ምናሔም ርዳታውን ለማግኘትና በመንግሥቱ ላይ ያለውን ይዞታ ለማጽናት ሲል፣ አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው።

20. ምናሔም ገንዘቡ እንዲዋጣ ያደረገው ከእስራኤል ሲሆን፣ ይህንንም ያደረገው ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ እያንዳንዱ ሀብታም አምሳ፣ አምሳ ሰቅል ብር እንዲያዋጣ በማስገደድ ነበር። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ በዚያች አገር አልቈየም፤ ተመልሶ ሄደ።

21. በምናሔም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

22. ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ፋቂስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

23. የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በአምሳኛው ዓመት፣ የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በሰማርያ ከተማ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ።

24. ፋቂስያስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

25. ከጦር አለቆቹ አንዱ የሆነው የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ አሤረበት፤ አምሳ የገለዓድ ሰዎች ይዞ በመሄድ፣ ሰማርያ ቤተ መንግሥት ባለው ምሽግ ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርያ ጋር ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

26. በፋቂስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

27. የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በሰማርያ ከተማ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሃያ ዓመትም ገዛ።

28. እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

29. በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን፣ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮን፣ አቤልቤትመዓካን፣ ያኖዋን፣ ቃዴስንና ሐጾርን፣ ገለዓድንና ገሊላን፣ የንፍታሌምንም ምድር ጭምር ያዘ። ሕዝቡንም ማርኮ ወደ አሦር ወሰደው።

30. ከዚያም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ አሤረበት፤ አደጋ ጥሎም ገደለው፤ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በነገሠ በሃያኛው ዓመትም ሆሴዕ በፋቁሔ እግር ተተክቶ ነገሠ።

31. በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸማቸውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

32. የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ።

33. ሲነግሥም ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ ኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ስትሆን፤ ኢየሩሳ ትባል ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 15