ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 13:11-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት ሁሉ አልራቀም፤ በዚያው ገፋበት።

12. ዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላ ሥራ፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያካሄደው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?።

13. ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓም በእግሩ ተተክቶ በዙፋኑ ተቀመጠ። ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ።

14. በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ ለሞት ባደረሰው ሕመም ታሞ ያጣጥር ነበር። የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ወርዶ አለቀሰለት፤ “ወየው አባቴን! ወየው አባቴን! ወየው የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” እያለም ጮኸ።

15. ኤልሳዕም፣ “አንድ ቀስትና ፍላጾች አምጣ” አለው፤ እርሱም አመጣ፤

16. የእስራኤልንም ንጉሥ፣ “ቀስቱን በእጅህ ያዘው” አለው፤ ቀስቱን በያዘውም ጊዜ ኤልሳዕ እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ።

17. ቀጥሎም፣ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለው፤ ከፈተውም፤ ኤልሳዕም፣ “በል አስፈንጥረው” አለው፤ አስፈነጠረውም፤ ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር የድል ቀስት!” ሶርያ ድል የምትሆንበት ቀስት!” አለ። ኤልሳዕም እንደ ገና “ሶርያውያንንም አፌቅ ላይ ፈጽመህ ድል ታደርጋቸዋለህ” አለው።

18. ቀጥሎም፣ “በል ቀስቶቹን ውሰድ” አለው፤ ንጉሡም ወሰደ። ኤልሳዕም፣ “መሬቱን ውጋ” አለው። እርሱም ሦስት ጊዜ ወግቶ አቆመ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 13