ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 13:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት፣ የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ሰባት ዓመትም ገዛ።

2. እርሱም የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ያሳተበትን ኀጢአት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ ከዚህ ድርጊቱም አልተመለሰም።

3. የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ አዛሄልና ልጁ ቤንሃዳድ በነበሩበት ዘመን ሁሉ አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው።

4. ከዚያም ኢዮአካዝ እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን እንዴት አድርጎ እንዳስጨነቀ አይቶአልና ልመናውን ሰማው።

5. ስለዚህ እግዚአብሔር ለእስራኤል የሚታደጋቸውን ሰው ሰጠ፤ እነርሱም ከሶርያውያን ጭቈና ተላቀቁ፤ እንደ ቀድሞውም በየድንኳናቸው መኖር ጀመሩ፤

6. ይሁን እንጂ እስራኤልን ካሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኀጢአት አልተመለሱም፤ በዚያው ገፉበት። የአሼራም ምስል ዐምድ በሰማርያ መመለኩ ቀጠለ።

7. ከኢዮአካዝ ሰራዊት የተረፈው ዐምሳ ፈረሰኞች፣ ዐሥር ሠረገሎችና ዐሥር ሺህ እግረኛ ወታደር ብቻ ነው፤ ይህ የሆነበትም ምክንያት የሶርያ ንጉሥ የቀረውን ስለ አጠፋውና እንደ ዐውድማ ብናኝ ስለ አደረገው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 13