ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 10:22-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ኢዩም የልብስ ቤቱን ኀላፊ፣ “ለበኣል አገልጋዮች ሁሉ አልባሳት አውጣ” አለው፤ እርሱም አልባሳቱን አወጣላቸው።

23. ከዚያም ኢዩ ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ጋር ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ገባ። የበኣልንም አገልጋዮች፣ “እንግዲህ የበኣል አገልጋዮች ብቻ እንጂ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እዚህ አብረዋችሁ አለመኖራቸውን አረጋግጡ” አላቸው።

24. ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለማቅረብ ገቡ። በዚህ ጊዜም ኢዩ፣ “በእጃችሁ አሳልፌ ከሰጠኋችሁ ሰዎች አንድ እንኳ እንዲያመልጥ ያደረገ በገመዱ ይገባበታል” ብሎ በማስጠንቀቅ ውጭ ሰማንያ ሰዎች አዘጋጅቶ ነበር።

25. ኢዩ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ ጠባቂዎቹንና የጦር አለቆቹን፣ “ግቡና ግደሏቸው፤ ማንም እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ። እነርሱም በሰይፍ ፈጇቸው፤ ጠባቂዎቹና የጦር ሹማምንቱም ሬሳውን በሙሉ ወደ ውጭ አውጥተው ጣሉ። ከዚያም ወደ ውስጠኛው የበኣል ቤተ ጣዖት ገቡ።

26. ከድንጋይ የተሠሩትንም ማምለኪያ ምስሎች ከበኣል ቤተ ጣዖት አውጥተው አቃጠሉ።

27. የበኣልን ማምለኪያ ምስል ቀጠቀጡ፤ የበኣልንም ቤተ አምልኮ አፈረሱ፤ ይህንንም ሕዝቡ እስከ ዛሬ ድረስ የኵስ መጣያው አድርጎታል።

28. በዚህ ሁኔታም ኢዩ የበኣልን አምልኮ ከእስራኤል አስወገደ።

29. ይሁን እንጂ ኢዩ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ በቤቴልና በዳን የወርቅ ጥጃዎች እንዲያመልኩ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልራቀም።

30. እግዚአብሔርም ኢዩን፣ “በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር ስላደረግህና በአክዓብም ቤት ላይ እንዲደርስ በልቤ ያለውን ሁሉ ስለፈጸምህ፤ ዘርህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣል” አለው።

31. ነገር ግን ኢዩ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ሕግ በፍጹም ልቡ ለመጠበቅ ጥንቃቄ አላደረገም፤ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልራቀምና።

32. በዚያ ዘመን እግዚአብሔር የእስራኤልን ምድር መቀናነስ ጀመረ። አዛሄልም እስራኤልን ዳር እስከ ዳር መታ።

33. ይኸውም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን የገለዓድን ምድር ሁሉ ሲሆን፣ ይህም በአርኖን ወንዝ አጠገብ ካለው ከአሮዔር አንሥቶ የጋድን፣ የሮቤልንና የምናሴን አገር ገለዓድንና ባሳንን ነበር።

34. የቀረው በኢዩ ዘመነ መንግሥት የሆነው፣ ያደረገውም ሁሉ፣ ያከናወነውም ሥራ በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

35. ኢዩ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአካዝም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

36. ኢዩ በሰማርያ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ የነገሠው ሃያ ስምንት ዓመት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 10