ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 10:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. “የጌታችሁ ልጆች ከእናንተ ጋር ስለሆኑ፣ ሠረገሎችና ፈረሶች፣ የተመሸገች ከተማና መሣሪያም ስላላችሁ፣ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ

3. ከጌታችሁ ልጆች መካከል ብልጫ ያለውንና ተገቢ ነው የምትሉትን መርጣችሁ በአባቱ ዙፋን አስቀምጡት። ከዚያም ስለ ጌታችሁ ቤት ተዋጉ።”

4. እነርሱ ግን እጅግ ፈርተው ነበርና፣ “ሁለት ነገሥታት ሊቋቋሙት ያልቻሉትን ሰው እኛ እንዴት ልንቋቋመው እንችላለን?” አሉ።

5. ስለዚህ የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፣ የከተማዪቱ ገዥ፣ ሽማግሌዎችና የልጆቹ ሞግዚቶች፣ “እኛ ያንተው አገልጋዮች ነን፤ ትእዛዝህን ሁሉ እንፈጽማለን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ አንተው አድርግ” በማለት ይህን መልእክት ለኢዩ ላኩ።

6. ከዚያም ኢዩ፣ “እንግዲህ የእኔ ወገን ከሆናችሁና ከታዘዛችሁኝ የጌታችሁን ልጆች ራስ ቈርጣችሁ ነገ በዚህ ሰዓት ይዛችሁልኝ ወደ ኢይዝራኤል እንድትመጡ” ሲል ደግሞ ጻፈላቸው።በዚህም ጊዜ ሰባው የንጉሡ ልጆች በከተማዪቱ ውስጥ ታዋቂ በሆኑ አሳዳጊዎቻቸው ዘንድ ነበሩ።

7. ደብዳቤውም በደረሳቸው ጊዜ፣ ሰዎቹ ሰባውን ልዑላን በሙሉ ወስደው ገደሏቸው። ራሳቸውንም በቅርጫት አድርገው ኢዩ ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ላኩ።

8. መልእክተኛው እንደ ደረሰም፣ ለኢዩ፣ “የንጉሡን ልጆች ራስ አምጥተዋል” ብሎ ነገረው። ከዚያም ኢዩ፣ “በከተማዪቱ መግቢያ በር ላይ ሁለት ቦታ ከምራችሁ እስከ ነገ ጧት ድረስ አቈዩአቸው” ብሎ አዘዘ።

9. በማግስቱም ጧት ኢዩ ወጥቶ በሕዝቡ ሁሉ ፊት በመቆም እንዲህ አለ፤ “እናንተ ንጹሓን ናችሁ፤ ጌታዬን ያሤርሁበትና የገደልሁት እኔ ነኝ። እነዚህን ሁሉ ግን የፈጃቸው ማን ነው?

10. እንግዲህ እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ቃል አንዲቱ እንኳ በምድር ላይ ወድቃ እንደማትቀር ዕወቁ። እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን ፈጽሞአል።”

11. ስለዚህ ኢዩ ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፣ ታላላቆቹን ሰዎች በሙሉ፣ የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው።

12. ከዚያም ኢዩ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ ቤትኤከድ ወደተባለው የበግ ጠባቂዎችም ቤት ሲደርስ፣

13. ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ሥጋ ዘመዶች ጥቂቶቹን አግኝቶ፣ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቃቸው፤እነርሱም፣ “እኛ የአካዝያስ ሥጋ ዘመዶች ነን፤ ንጉሣዊውን ቤተ ሰብና የእቴጌይቱን ልጆች ለመጠየቅ ወደዚህ ወርደን መጥተናል” አሉ።

14. እርሱም፣ “ከነሕይወታቸው ያዟቸው!” ሲል አዘዘ፤ ስለዚህ ከነሕይወታቸው ወስደው በቤት ኤከድ ጒድጓድ አጠገብ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሏቸው፤ አንድ እንኳ አላስቀረም።

15. ከዚያም ተነሥቶ ሲሄድ የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ወደ እርሱ ሲመጣ መንገድ ላይ አገኘው። ኢዩም ሰላምታ ሰጥቶት “ልቤ ለልብህ ታማኝ የሆነውን ያህል ያንተስ ልብ ለልቤ እንዲሁ ታማኝ ነውን?” ሲል ጠየቀው።ኢዮናዳብም፣ “አዎን፤ ነው!” ብሎ መለሰ።ኢዩም፣ “እንግዲያውስ እጅህን ስጠኝ” አለው። እጁንም ሰጠው፤ ከዚያም ኢዩ ደግፎ ወደ ሠረገላው አወጣው።

16. ኢዩም፣ “በል አብረን እንሂድና ለእግዚአብሔር ያለኝን ቅናት እይልኝ” አለው፤ ከዚያም በሠረገላው ይዞት ሄደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 10