ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 10:15-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ከዚያም ተነሥቶ ሲሄድ የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ወደ እርሱ ሲመጣ መንገድ ላይ አገኘው። ኢዩም ሰላምታ ሰጥቶት “ልቤ ለልብህ ታማኝ የሆነውን ያህል ያንተስ ልብ ለልቤ እንዲሁ ታማኝ ነውን?” ሲል ጠየቀው።ኢዮናዳብም፣ “አዎን፤ ነው!” ብሎ መለሰ።ኢዩም፣ “እንግዲያውስ እጅህን ስጠኝ” አለው። እጁንም ሰጠው፤ ከዚያም ኢዩ ደግፎ ወደ ሠረገላው አወጣው።

16. ኢዩም፣ “በል አብረን እንሂድና ለእግዚአብሔር ያለኝን ቅናት እይልኝ” አለው፤ ከዚያም በሠረገላው ይዞት ሄደ።

17. ኢዩ ወደ ሰማርያ በደረሰ ጊዜ፣ ከአክዓብ ቤተ ሰብ በዚያ የቀረውን ሁሉ ገደለ። ለነቢዩ ለኤልያስ በተነገረውም የእግዚአብሔር ቃል መሠረት አጠፋቸው።

18. ከዚያም ኢዩ ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አለ፤ “አክዓብ በኣልን ያገለገለው በጥቂቱ ነው፤ ኢዩ ግን ይበልጥ ያገለግለዋል።

19. አሁንም የበኣልን ነቢያት ሁሉ አገልጋዮቹንና ካህናቱንም በሙሉ ጥሩልኝ። ለባኣል ትልቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ አንድ ሰው እንኳ እንዳይቀር። የማይመጣ ሰው ቢኖር ግን በሕይወት አይኖርም፤ ኢዩ ግን ይህን ማድረጉ የበኣልን አገልጋዮች ለማጥፋት ተንኰል መፍጠሩ ነበር።

20. ኢዩም፣ “ለበኣል ክብር ጉባኤ ጥሩ” አለ፤ እነርሱም ይህንኑ ለሕዝቡ አስታወቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 10