ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 5:8-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. በዚያም ዕለት ዳዊት፣ “ኢያቡሳውያንን ድል ማድረግ የሚፈልግ፣ የዳዊት ጠላቶች ወደሚሆኑ፣ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያው ሽቅብ መውጣት አለበት” አለ። እንግዲህ፣ “ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” ያሉት ለዚህ ነው።

9. ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባት።

10. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ ዳዊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ሄደ።

11. በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ አናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችን አብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት።

12. እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን እንዳሰፋለት ዳዊት ዐወቀ።

13. ዳዊት ከኬብሮን ከሄደ በኋላ፣ ከበፊቶቹ በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ሌሎች ቁባቶች አስቀመጠ፤ ሚስቶችም አገባ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት።

14. በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣

15. ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ናፍያ፣

16. ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባላሉ።

17. ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ለመፈለግ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊት ግን ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ።

18. በዚህ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ።

19. ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ፍልስጥኤማውያንን ወጥቼ ልውጋቸው? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ?” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ሂድ፤ በእርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው።

20. ስለዚህም ዳዊት ወደ በአልፐራሲም ሄዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው። እርሱም “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ፣ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” አለ። ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም በአልፐራሲም ተባለ።

21. ፍልስጥኤማውያንም ጣዖቶቻቸውን ትተው ሸሽተው ስለ ነበር፣ ዳዊትና ሰዎቹ ወስደው አቃጠሏቸው።

22. ፍልስጥኤማውያን እንደ ገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ።

23. ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በስተ ኋላቸው በኩል በመክበብ በበለሳኑ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ በቀጥታ ወዳሉበት አትውጣ፤

24. በበለሳኑ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ጒዞ ድምፅ ስትሰማም፣ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት ቀድሞህ ወጥቶአል ማለት ነውና በዚያን ጊዜ በፍጥነት ወደ ፊት ሂድ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 5