ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 5:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ንጉሡና ሰዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ለመውጋት ወደዚያ ሄዱ። ኢያቡሳውያንም፣ “ዳዊት እዚህ ሊገባ አይችልም” ብለው ስላሰቡ ዳዊትን፣ “ዕውሮችና አንካሶች እንኳ ይከለክሉሃልና ወደዚህች አትገባም” አሉት።

7. ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን ዐምባ ያዘ፤ ይህችም የዳዊት ከተማ የተባለችው ናት።

8. በዚያም ዕለት ዳዊት፣ “ኢያቡሳውያንን ድል ማድረግ የሚፈልግ፣ የዳዊት ጠላቶች ወደሚሆኑ፣ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያው ሽቅብ መውጣት አለበት” አለ። እንግዲህ፣ “ ‘አንካሶችና ዕውሮች’ ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” ያሉት ለዚህ ነው።

9. ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባት።

10. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ ዳዊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ሄደ።

11. በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ አናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችን አብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት።

12. እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን እንዳሰፋለት ዳዊት ዐወቀ።

13. ዳዊት ከኬብሮን ከሄደ በኋላ፣ ከበፊቶቹ በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ሌሎች ቁባቶች አስቀመጠ፤ ሚስቶችም አገባ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት።

14. በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣

15. ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ናፍያ፣

16. ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባላሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 5