ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 4:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ የወራሪ ጭፍራ ቡድን መሪዎች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ አንዱ በዓና ሌላው ደግሞ ሬካብ ይባሉ ነበር። እነርሱም ከብንያም ነገድ የብኤሮት ተወላጅ የሆነው የሬሞን ልጆች ነበሩ፤ ብኤሮት ከብንያም ክፍል እንደ አንዱ ትቈጠራለች።

3. የብኤሮት ሕዝብ ወደ ጌቴም በመሸሽ እስከ ዛሬም በመጻተኝነት እዚያው ይኖራልና።

4. የሳኦል ልጅ ዮናታን ሁለት እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው። እርሱም የሳኦልና የዮናታን አሟሟት ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረ። ሽባ የሆነውንም በዚህ ጊዜ ሞግዚቱ አንሥታው በጥድፊያ ስትሸሽ በመውደቁ ነው። ስሙም ሜምፊቦስቴ ይባል ነበር።

5. በዚህ ጊዜ የብኤሮታዊው የሬሞን ልጆች ሬካብና በዓና ወደ ኢያቡስቴ ቤት ለመሄድ ዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ፣ ሙቀት ሲሆን እኩለ ቀን ላይ ደረሱ፤

6. ስንዴ እንደሚፈ ልግም ሰው ሆነው ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ሆዱ ላይ ወጉት። ከዚያም ሬካብና ወንድሙ በዓና ሹልክ ብለው ወጡ።

7. ወደ ቤቱ ውስጥ የገቡት ኢያቡስቴ በመኝታ ክፍሉ ውስጥ ተኝቶ ሳለ ነበር፤ ወግተው ከገደሉትም በኋላ ራሱን ቈርጠው በመውሰድ፣ ሌሊቱን ሁሉ በዓረባ መንገድ ተጓዙ።

8. የኢያቡስቴንም ራስ ወደ ኬብሮን ዳዊት ዘንድ አምጥተው ንጉሡን፣ “አንተን ሊገድል ይፈልግ የነበረው የጠላትህ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ፤ እነሆ እግዚአብሔር በዛሬው ቀን ስለ ጌታዬ ስለ ንጉሡ ሳኦልንና ዘሩን ተበቅሎአል” አሉት።

9. ዳዊትም ለብኤሮታዊው ለሬሞን ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ ‘ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን፣

10. የምሥራች ያመጣልኝ መስሎት፣ ‘እነሆ ሳኦል ሞተ’ ብሎ የነገረኝን ሰው ይዤ ጺቅላግ ላይ ገደልሁት፤ እንግዲህ ለዚያ ሰው ስላመጣው ምሥራች የሸለምሁት ይህን ነበር።

11. ታዲያ በገዛ ቤቱ፣ በገዛ ዐልጋው ላይ ዐርፎ የተኛውን ንጹሕ ሰው የገደሉትን ክፉ ሰዎች እንዴት የባሰ ቅጣት አይገባቸውም? ደሙን ከእጃችሁ መፈለግ፣ እናንተን ከምድሪቱ ማጥፋት የለብኝምን?”

12. ስለዚህም ዳዊት የራሱን ሰዎች አዘዘ፤ እነርሱንም ገደሏአቸው፤ እጅና እግራቸውንም ቈርጠው በኬብሮን ካለው ኵሬ አጠገብ ሰቀሏቸው። ነገር ግን የኢያቡስቴን ራስ ወስደው ኬብሮን በሚገኘው በአበኔር መቃብር አጠገብ ቀበሩት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 4