ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 20:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚህ ጊዜ የቢክሪ ልጅ ስሙ ሳቤዔ የተባለ አንድ ምናምንቴ ብንያማዊ በዚያ ነበረ፤ እርሱም መለከት ነፍቶ እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “እኛ ከዳዊት ድርሻ የለንም፤ ከእሴይም ልጅ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ፤ እያንዳንድህ ወደ ድንኳንህ ተመለስ!”

2. ስለዚህ የእስራኤል ሰው ሁሉ ዳዊትን ከድቶ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ተከተለ። የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ አንሥቶ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ከንጉሣቸው ሳይ ለዩ አብረውት ሄዱ።

3. ዳዊት ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መንግሥቱ በተመለሰ ጊዜ፤ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ትቶአቸው የሄደውን ዐሥሩን ቁባቶቹን ወሰደ፤ በአንድ ቤትም ውስጥ እንዲጠበቁ አደረገ። ቀለብ ሰጣቸው፤ ይሁን እንጂ ወደ እነርሱ አልገባም ነበር፤ እነርሱም እስከ ሞቱበት ጊዜ ድረስ መበለት ሆነው፣ ለብቻቸው ተገልለው ተቀመጡ።

4. ከዚያም ንጉሡ አሜሳይን፣ “የይሁዳ ሰዎች ሁሉ በሦስት ቀን ውስጥ፣ ወደ እኔ እንዲመጡ ጥራልኝ፤ አንተ ራስህም ተገኝ” አለው።

5. አሜሳይ ይሁዳን ለመጥራት ሄደ፤ ነገር ግን ንጉሡ ከወሰነው ጊዜ በላይ ቈየ።

6. ዳዊትም አቢሳን፣ “ከአቤሴሎም ይልቅ አሁን የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ የበለጠ ጒዳት ሊያደርስብን ስለ ሆነ የጌታህን ሰዎች ይዘህ አሳደው፤ ያለዚያ የተመሸገ ከተማ አግኝቶ ያመልጠናል” አለው።

7. ስለዚህ የኢዮአብ ሰዎች፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ሌሎች ኀያላን ጦረኞች በሙሉ በአቢሳ አዛዥነት ወጡ፤ ከኢየሩሳሌም የወጡትም የቢክሪ ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ነበር።

8. በገባዖን ከታላቁ ቋጥኝ አጠገብ ሳሉ፣ አሜሳይ ሊገናኛቸው መጣ፤ ኢዮአብ የጦር ሜዳ ልብሱን ለብሶ ሰይፉን ከሰገባው በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር፤ ወደ ፊት ራመድ እንዳለም ሰይፉ ከሰገባው ወጥቶ ወደቀ።

9. ኢዮአብም አሜሳይን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እንደምንድን ነህ?” አለው፤ ከዚያም አሜሳይን የሚስም መስሎ በቀኝ እጁ ጢሙን ያዘው።

10. አሜሳይ ግን በኢዮአብ እጅ ሰይፍ መኖሩን ልብ ስላላለ ጥንቃቄ አላደረገም፤ ስለዚህ ኢዮአብ ሰይፉን ሆዱ ላይ ሻጠበት፤ አንጀቱም መሬት ላይ ተዘረገፈ፤ ከዚያም ኢዮአብ መድገም ሳያስፈልገው፣ አሜሳይ በዚያው ሞተ። ከዚህ በኋላ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ፣ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ማሳደድ ጀመሩ።

11. በአሜሳይ ሬሳ አጠገብ ከቆሙት ከኢዮአብ ሰዎች አንዱ፤ “ኢዮአብን የሚወድ፣ የዳዊትም የሆነ ሁሉ ኢዮአብን ይከተል!” አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 20