ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 2:14-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ከዚያም አበኔር፣ ኢዮአብን፣ “ከእናንተም ከእኛም ጒልማሶች ይነሡና በፊታችን በጨበጣ ውጊያ ይጋጠሙ” አለው።ኢዮአብም፣ “ይሁን እሺ ይጋጠሙ” ብሎ መለሰ።

15. ስለዚህ ከብንያም ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፣ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተነሥተው ተቈጠሩ።

16. ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጐኑ እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ቦታ “የሰይፍ ምድር” ተባለ።

17. የዚያን ዕለቱ ጦርነት እጅግ ከባድ ነበር፤ አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት ሰዎች ድል ሆኑ።

18. ሦስቱ የጽሩያ ወንዶች ልጆች ኢዮአብ፣ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤

19. ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል አበኔርን ተከታተለው።

20. አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፣ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት።

21. ከዚያም አበኔር፣ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጒልማሳ ይዘህ መሣሪያውን ንጠቀው” አለው። አሣሄል ግን እርሱን መከታተሉን አልተወም ነበር።

22. እንደ ገናም አበኔር፣ “እኔን መከታተል ብትተው ይሻልሃል፤ እኔስ ለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት ቀና ብዬ እንዴት አያለሁ?” አለው።

23. አሣሄል ግን መከታተሉን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፣ ጦሩም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወዲያው ሞተ። እያንዳንዱም አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር።

24. ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ እያሳደዱም ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጋይ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኰረብታ ሲደርሱ ፀሓይ ጠለቀች።

25. ከዚያም የብንያም ሰዎች ወደ አበኔር ተሰብስበው ግንባር በመፍጠር በኰረብታው ጫፍ ላይ ተሰለፉ።

26. አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፣ “ይህ ሰይፍ ዘላለም ማጥፋት አለበትን? ውጤቱ መራራ መሆኑን አንተስ ሳታውቀው ቀርተህ ነውን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን እንዲያቆሙ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?” አለው።

27. ኢዮአብም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፣ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር” ብሎ መለሰ።

28. ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተው፤ ውጊያውም በዚሁ አበቃ።

29. አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓረባን አልፈው ሄዱ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን በመሻገር ቢትሮንን ሁሉ ዐልፈው ወደ መሃናይም መጡ።

30. ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፣ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጥፋታቸው ታወቀ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 2