ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 19:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ለኢዮአብ፣ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰ እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው።

2. ንጉሡ፣ “ስለ ልጁ አዝኖአል” መባሉን በዚያ ቀን ሰራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሰራዊት ዘንድ ወደ ሐዘን ተለውጦ ዋለ።

3. በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ተሸማቆ ወደ ከተማ ገባ።

4. ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፤ ልጄን! ወየው ልጄን!” እያለ ጮኸ።

5. ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፣ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፣ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍ ረሃቸዋል።

6. የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ።

7. በል አሁን ተነሥተህ ውጣና ሰዎችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያስከትልብሃል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 19