ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 18:5-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ንጉሡም ኢዮአብን፣ አቢሳንና ኢታይን፣ “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ ልጄ በአቤሴሎም ላይ ጒዳት እንዳታደርሱበት” ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡ ልጁን አቤሴሎምን አስመልክቶ ለእያንዳንዱ አዛዥ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰራዊቱ ሁሉ ሰማ።

6. ሰራዊቱ እስራኤልን ለመውጋት ተሰልፎ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ጦርነቱም በኤፍሬም ደን ውስጥ ሆነ።

7. እዚያም የእስራኤል ሰራዊት በዳዊት ሰዎች ተመታ፤ በዚያም ቀን ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ሃያ ሺህም ሰው ተገደለ።

8. ውጊያው በገጠሩ ሁሉ ተስፋፋ፤ በዚያን ቀን ሰይፍ ከጨረሰው ይልቅ ጫካ ውጦ ያስቀረው ሰው በለጠ።

9. በዚህ ጊዜ አቤሴሎም ከዳዊት ሰዎች ጋር ድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎም በበቅሎ ተቀምጦ ይሄድ ስለ ነበር፣ በቅሎዋ ጥቅጥቅ ያለ ቅርንጫፍ ባለው ትልቅ ወርካ ሥር በምታልፍበት ጊዜ፣ የአቤሴሎም ራስ በዛፉ ቅርንጫፍ ተያዘ፤ የተቀመጠበትም በቅሎ በሥሩ ስታልፍ፣ እርሱ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠልጥሎ ቀረ።

10. አንድ ሰው ይህን አይቶ ለኢዮአብ፣ “እነሆ፤ አቤሴሎም በባሉጥ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት” አለው።

11. ኢዮአብም ይህን የነገረውን ሰው፣ “ምን አልህ! ካየኸው ታዲያ ለምንድን ነው ያኔውኑ መተህ መሬት ላይ ያልጣልኸው? ይህን አድርገህ ቢሆን ኖሮ፣ ዐሥር ሰቅል ጥሬ ብርና የጀግና ሰው ቀበቶም እሸልምህ ነበር” አለው።

12. ሰውየው ግን እንዲህ አለ፤ “እኛ እየሰማን ንጉሡ፣ ‘ወጣቱ አቤሴሎም ጒዳት እንዳያገኘው ስለ እኔ ብላችሁ ጠብቁት’ ብሎ አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ያዘዛችሁ ስለ ሆነ፣ አንድ ሺህ ሰቅል ጥሬ ብር በእጄ ላይ ቢመዘንልኝ እንኳ፣ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሣም።

13. በሌላ በኩል ደግሞ በነፍሴ ቈርጬ ሕይወቱን ባጠፋው ኖሮ፣ ከንጉሡ ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ፣ አንተም ራስህ አትቀርበኝም ነበር” ብሎ መለሰለት።

14. ኢዮአብም፣ “ከእንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከአንተ ጋር ጊዜ ማጥፋት አልችልም” አለው፤ ስለዚህ በእጁ ሦስት ጦር ይዞ ሄደና አቤሴሎም እዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት እያለ፣ ወርውሮ በልቡ ላይ ተከላቸው።

15. እንዲሁም ከኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ዐሥሩ አቤሴሎምን በመክበብ ወግተው ገደሉት።

16. ከዚያም ኢዮአብ ቀንደ መለከት ነፍቶ ስለ ከለከላቸው፣ ሰራዊቱ እስራኤልን ማሳደዱን አቆመ።

17. አቤሴሎምን ጫካ ወስደው በትልቅ ጒድጓድ ውስጥ ወርውረው ጣሉት፤ በላዩም ትልልቅ ድንጋይ ከመሩበት። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ የቤታቸው ሸሹ።

18. አቤሴሎም፣ “ስሜን የሚያስጠራ ልጅ የለኝም” በማለት መታሰቢያ እንዲሆነው በሕይወት እያለ የንጉሥ ሸለቆ በተባለው ስፍራ በራሱ ስም ሐውልት አቁሞ ስለ ነበር፣ እስከ ዛሬ ድረስ የአቤሴሎም ሐውልት ተብሎ ይጠራል።

19. በዚህ ጊዜ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ፣ “እግዚአብሔር ጠላቶቹን የተበቀለለት መሆኑን ሮጬ ሄጄ ለንጉሡ የምሥራች ልንገረው” አለ።

20. ኢዮአብም፣ “ዛሬ የምሥራቹን ወሬ የምትወስድለት አንተ አይደለህም፤ የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ፣ ዛሬ ሳይሆን፣ የምሥራቹን ሌላ ጊዜ ታደርስለታለህ” አለው።

21. ከዚያም ኢዮአብ ለኢትዮጵያዊው፣ “ሂድና ያየኸውን ለንጉሡ ንገር” አለው፤ ኢትዮጵያዊውም ኢዮአብን እጅ ነሥቶ እየሮጠ ሄደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 18