ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 18:16-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ከዚያም ኢዮአብ ቀንደ መለከት ነፍቶ ስለ ከለከላቸው፣ ሰራዊቱ እስራኤልን ማሳደዱን አቆመ።

17. አቤሴሎምን ጫካ ወስደው በትልቅ ጒድጓድ ውስጥ ወርውረው ጣሉት፤ በላዩም ትልልቅ ድንጋይ ከመሩበት። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ የቤታቸው ሸሹ።

18. አቤሴሎም፣ “ስሜን የሚያስጠራ ልጅ የለኝም” በማለት መታሰቢያ እንዲሆነው በሕይወት እያለ የንጉሥ ሸለቆ በተባለው ስፍራ በራሱ ስም ሐውልት አቁሞ ስለ ነበር፣ እስከ ዛሬ ድረስ የአቤሴሎም ሐውልት ተብሎ ይጠራል።

19. በዚህ ጊዜ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ፣ “እግዚአብሔር ጠላቶቹን የተበቀለለት መሆኑን ሮጬ ሄጄ ለንጉሡ የምሥራች ልንገረው” አለ።

20. ኢዮአብም፣ “ዛሬ የምሥራቹን ወሬ የምትወስድለት አንተ አይደለህም፤ የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ፣ ዛሬ ሳይሆን፣ የምሥራቹን ሌላ ጊዜ ታደርስለታለህ” አለው።

21. ከዚያም ኢዮአብ ለኢትዮጵያዊው፣ “ሂድና ያየኸውን ለንጉሡ ንገር” አለው፤ ኢትዮጵያዊውም ኢዮአብን እጅ ነሥቶ እየሮጠ ሄደ።

22. የሳዶቅ ልጅ አኪማአስም እንደ ገና ኢዮአብን፣ “የመጣው ይምጣ፤ እባክህ ኢትዮጵያዊውን ተከትየው ልሩጥ” አለው።ኢዮአብ ግን፣ “ልጄ ሆይ፣ መሄድ ለምን አስፈለገህ? ሽልማት የሚያሰጥህ ምን የምሥራች ይዘህ ነው?” ብሎ መለሰለት።

23. አኪማአስም፣ “የመጣው ይምጣ፤ መሄድ እፈልጋለሁ” አለ።ስለዚህም ኢዮአብ፣ “እንግዲያውማ ሩጥ!” አለው። ከዚያም አኪማአስ በሜዳው መንገድ ሮጦ ኢትዮጵያዊውን ቀድሞት ሄደ።

24. ዳዊት በውስጠኛውና በውጭኛው በሮች መካከል ተቀምጦ ሳለ፣ ጠባቂው ቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ጣራ ወጥቶ ወደ ውጭ ሲመለከት አንድ ሰው ብቻውን ሲሮጥ አየ።

25. ጠባቂውም ተጣራና ይህንኑ ለንጉሡ ነገረው፤ንጉሡም፣ “ብቻውን ከሆነ መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ። ሰውየውም እየቀረበ መጣ።

26. ከዚያም ጠባቂው ሌላ ሰው ሲሮጥ አይቶ፣ ዘበኛውን ተጣራና፣ “እነሆ ሌላም ሰው ብቻውን እየሮጠ በመምጣት ላይ ነው!” አለ።ንጉሡም፣ “ይኸኛውም መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ።

27. ጠባቂውም፣ “የመጀመሪያው ሰው ሩጫ የሳዶቅን ልጅ የአኪማአስን ሩጫ ይመስለኛል” አለ።ንጉሡም፣ “እርሱማ ጥሩ ሰው ነው፤ የምሥራች ሳይዝ አይመጣም” አለ።

28. አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን፣ “ሁሉም ነገር ተሳክቶአል” አለ፤ ከዚያም ወደ መሬት ለጥ ብሎ በንጉሡ ፊት እጅ ነሣና፣ “በጌታዬ በንጉሡ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!” አለ።

29. ንጉሡም፣ “ብላቴናው አቤሴሎም ደኅና ነውን?” ሲል ጠየቀ።አኪማአስም፣ “ኢዮአብ የንጉሡን አገልጋይና እኔንም ባሪያህን ሊልክ ሲል፣ ትልቅ ሁካታ አይቻለሁ፤ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም” ብሎ መለሰ።

30. ንጉሡም፣ “እልፍ በልና ቁም” አለው፤ ስለዚህ እልፍ ብሎ ቆመ።

31. ከዚያም ኢትዮጵያዊው ደርሶ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ የምሥራች! ዛሬ እግዚአብሔር ከተነሡብህ ጠላቶችህ ሁሉ ታድጎሃል” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 18