ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 15:2-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ሆን ብሎ ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጒዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፣ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፣ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፣ “አገልጋይህ ከአንዱ የእስራኤል ነገዶች ነው” ብሎ ይመልስለታል።

3. ከዚያም አቤሴሎም፣ “ተመልከት! ጒዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ የትኛው የንጉሥ እንደራሴ ነው ታዲያ የሚያይልህ?” ይለዋል።

4. ቀጠል አድርጎም፣ “ምነው ዳኛ ሆኜ በምድሪቱ ላይ በተሾምሁ አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ እየመጣ ፍትሕ እንዲያገኝ አደርገው ነበር” ይል ነበር።

5. እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፣ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር።

6. አቤሴሎም ፍትሕ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጣውን እስራኤላዊ ሁሉ የሚቀርበው በዚህ መንገድ ስለ ነበር፣ የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።

7. ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ፤

8. እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በጌሹር ሳለሁ ‘እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፣ በኬብሮን ለእግዚአብሔር እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 15