ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 13:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ፤ አምኖንም፣ “እኅቴ ትዕማር መጥታ፣ እያየሁ ሁለት እንጀራ ጋግራ በእጇ እንድታጐርሰኝ እለምንሃለሁ” ብሎ ጠየቀው።

7. ዳዊትም፣ “ወንድምሽ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ እንድታዘጋጂለት” በማለት ለትዕማር እንዲነግሯት ወደ ቤተ መንግሥቱ ላከ።

8. ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደ ተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካች በኋላ እያየ አዘጋጅታ ጋገረችው፤

9. ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ እንጀራውን አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም።አምኖንም፣ “ሰውን ሁሉ ከዚህ አስወጡልኝ” አለ፤ ያለውም ሰው ሁሉ ትቶት ወጣ።

10. ከዚያም አምኖን ትዕማርን፣ “እንድታጐርሺኝ ምግቡን እዚሁ መኝታ ክፍሌ አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም ያዘጋጀችውን እንጀራ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወዳለበት መኝታ ክፍል ገባች።

11. ነገር ግን ምግቡን ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና፣ “እህቴ ነዪ አብረን እንተኛ” አላት።

12. እርሷም እንዲህ አለችው፤ “እባክህ ወንድሜ ተው አይሆንም! አታስገድደኝ፤ እንዲህ ያለው ነገር በእስራኤል ተደርጎ አያውቅም፤ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አታድርግ።

13. እኔስ እንዴት እሆናለሁ? ነውሬንስ ተሸክሜ የት እገባለሁ? አንተስ ብትሆን በእስራኤል ከወራዳዎቹ እንደ አንዱ መቈጠርህ አይደለምን? እባክህ ለንጉሡ ንገረው፤ እንዳላገባህም አይከለክለኝም።”

14. እርሱ ግን ሊሰማት አልፈለገም፤ ከእርሷ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበር፣ በግድ አስነወራት፤ ከእርሷም ጋር ተኛ።

15. ከዚያም አምኖን እጅግ ጠላት፤ እንዲያውም ቀድሞ ካፈቀራት የበለጠ ጠላት። አምኖንም፣ “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት።

16. እርሷም፣ “ይህ አይሆንም! እኔን አስወጥቶ መስደድ፣ አስቀድመህ ካደረስህብኝ በደል የባሰ መፈጸምህ ነው” አለችው። እርሱ ግን አልተቀበላትም፤

17. በግል የሚያገለግለውን ወጣት ጠርቶ፣ “ይህቺን ሴት ከዚህ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 13