ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 13:2-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. አምኖን እኅቱን ትዕማርን ከማፍቀሩ የተነሣ እስኪታመም ድረስ ተጨነቀ፤ ድንግል ስለሆነች እርሷን ማግኘት የማይቻል ሆኖ አግኝቶታልና።

3. አምኖን ኢዮናዳብ የተባለ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ነው። ኢዮናዳብ እጅግ ተንኰለኛ ሰው ነበር።

4. አምኖንንም፣ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፤ ሰውነትህ ቀን በቀን የሚከሳበትን ምክንያት ለምን አትነግረኝም?” ሲል ጠየቀው።አምኖንም፣ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው።

5. ኢዮናዳብም፣ “እንግዲያው ‘ታምሜአለሁ’ ብለህ ዐልጋ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣም፣ ‘እኅቴ ትዕማር መጥታ የምበላውን ነገር ብትሰጠኝ ደስ ይለኛል፤ መብሉንም እዚሁ አጠገቤ ሆና እያየሁ አዘጋጅታ በእጇ እንድታጐርሰኝ እባክህ ፍቀድልኝ ብለህ ንገረው” አለው።

6. ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ፤ አምኖንም፣ “እኅቴ ትዕማር መጥታ፣ እያየሁ ሁለት እንጀራ ጋግራ በእጇ እንድታጐርሰኝ እለምንሃለሁ” ብሎ ጠየቀው።

7. ዳዊትም፣ “ወንድምሽ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ እንድታዘጋጂለት” በማለት ለትዕማር እንዲነግሯት ወደ ቤተ መንግሥቱ ላከ።

8. ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደ ተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካች በኋላ እያየ አዘጋጅታ ጋገረችው፤

9. ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ እንጀራውን አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም።አምኖንም፣ “ሰውን ሁሉ ከዚህ አስወጡልኝ” አለ፤ ያለውም ሰው ሁሉ ትቶት ወጣ።

10. ከዚያም አምኖን ትዕማርን፣ “እንድታጐርሺኝ ምግቡን እዚሁ መኝታ ክፍሌ አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም ያዘጋጀችውን እንጀራ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወዳለበት መኝታ ክፍል ገባች።

11. ነገር ግን ምግቡን ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና፣ “እህቴ ነዪ አብረን እንተኛ” አላት።

12. እርሷም እንዲህ አለችው፤ “እባክህ ወንድሜ ተው አይሆንም! አታስገድደኝ፤ እንዲህ ያለው ነገር በእስራኤል ተደርጎ አያውቅም፤ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አታድርግ።

13. እኔስ እንዴት እሆናለሁ? ነውሬንስ ተሸክሜ የት እገባለሁ? አንተስ ብትሆን በእስራኤል ከወራዳዎቹ እንደ አንዱ መቈጠርህ አይደለምን? እባክህ ለንጉሡ ንገረው፤ እንዳላገባህም አይከለክለኝም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 13