ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 13:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ከዚያም አምኖን ትዕማርን፣ “እንድታጐርሺኝ ምግቡን እዚሁ መኝታ ክፍሌ አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም ያዘጋጀችውን እንጀራ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወዳለበት መኝታ ክፍል ገባች።

11. ነገር ግን ምግቡን ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና፣ “እህቴ ነዪ አብረን እንተኛ” አላት።

12. እርሷም እንዲህ አለችው፤ “እባክህ ወንድሜ ተው አይሆንም! አታስገድደኝ፤ እንዲህ ያለው ነገር በእስራኤል ተደርጎ አያውቅም፤ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አታድርግ።

13. እኔስ እንዴት እሆናለሁ? ነውሬንስ ተሸክሜ የት እገባለሁ? አንተስ ብትሆን በእስራኤል ከወራዳዎቹ እንደ አንዱ መቈጠርህ አይደለምን? እባክህ ለንጉሡ ንገረው፤ እንዳላገባህም አይከለክለኝም።”

14. እርሱ ግን ሊሰማት አልፈለገም፤ ከእርሷ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበር፣ በግድ አስነወራት፤ ከእርሷም ጋር ተኛ።

15. ከዚያም አምኖን እጅግ ጠላት፤ እንዲያውም ቀድሞ ካፈቀራት የበለጠ ጠላት። አምኖንም፣ “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት።

16. እርሷም፣ “ይህ አይሆንም! እኔን አስወጥቶ መስደድ፣ አስቀድመህ ካደረስህብኝ በደል የባሰ መፈጸምህ ነው” አለችው። እርሱ ግን አልተቀበላትም፤

17. በግል የሚያገለግለውን ወጣት ጠርቶ፣ “ይህቺን ሴት ከዚህ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው።

18. ስለዚህም አገልጋዩ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ ጌጠኛ የሆነና በዚያን ጊዜ ድንግል የሆኑት የንጉሥ ልጆች የሚለብሱትን ዐይነት ልብስ ለብሳ ነበር።

19. ትዕማርም በራሷ ላይ ዐመድ ነሰነሰች፤ ጌጠኛ ልብሷን ቀደደች፤ ከዚያም እጇን በራሷ ላይ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች።

20. ወንድሟ አቤሴሎምም፣ “ያ ወንድምሽ አምኖን ካንቺ ጋር ነበርን? እኅቴ ሆይ፣ አሁን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ስለ ሆነ፤ ነገሩን በልብሽ አትያዢው” አላት። ትዕማርም በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ብቸኛ ሴት ሆና ኖረች።

21. ንጉሥ ዳዊት ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 13