ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 10:8-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. አሞናውያን ወጥተው በከተማቸው መግቢያ በር ላይ ተሰለፉ፤ የሱባና የረአብ ሶርያውያን እንዲሁም የጦብና የመዓካ ሰዎች ለብቻ ሜዳው ላይ ተሰለፉ።

9. ኢዮአብም ከፊትና ከኋላው ጦር እንደ ከበበው ባየ ጊዜ፣ በእስራኤል ጀግንነታቸው ከታወቀው ጥቂቶቹን መርጦ በሶርያውያን ግንባር አሰለፋቸው።

10. የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ ሥር መድቦ በአሞናውያን ግንባር አሰለፋቸው።

11. ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ ሶርያውያን የሚያይሉብኝ ከሆነ አንተ መጥተህ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን የሚያይሉብህ ከሆነ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ።

12. እንግዲህ በርታ፤ ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች በጀግንነት እንዋጋ፤ እግዚአብሔርም በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ።

13. ከዚያም ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሠ፤ ሶርያውያንም ከፊቱ ሸሹ።

14. ሶርያውያን መሸሻቸውን አሞናውያን ባዩ ጊዜ፣ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ውስጥ ገቡ። ስለዚህም ኢዮአብ አሞናውያንን መውጋቱን አቁሞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

15. ሶርያውያን በእስራኤላውያን እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ፣ እንደ ገና ተሰባሰቡ።

16. አድርአዛር መልክተኞችን ሰዶ ከወንዙ ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጣ፤ እነርሱም በአድርአዛር ሰራዊት አዛዥ በሶባክ መሪነት ወደ ኤላም ሄዱ።

17. ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ መላውን እስራኤልን ሰበሰበ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ዔላም ሄደ። ሶርያውያንም ለጦርነት ተሰልፈው ዳዊትን በግንባር ገጠሙት፤

18. ይሁን እንጂ ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ሰባት መቶ ሠረገለኞችንና አርባ ሺህ እግረኛ ወታደሮች ገደለባቸው። እንዲሁም የሰራዊታቸውን አዛዥ ሶባክን አቍስሎት ስለ ነበር፣ እዚያው ሞተ።

19. በአድርአዛር ሥር የነበሩት ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል መሸነፋቸውን ባዩ ጊዜ ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም መሠረቱ፤ ተገዙላቸውም።ስለዚህም ሶርያውያን ከዚያ በኋላ አሞናውያንን መርዳት ፈሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 10