ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 9:29-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. ሌሎቹ ሌዋውያን ደግሞ ዕቃዎቹንና የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት፣ ዱቄቱን፣ የወይን ጠጁን፣ የወይራ ዘይቱን፣ ዕጣኑን፣ የሽቱውን ቅመማ ቅመም እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።

30. ከካህናቱም አንዳንዶቹ የሽቱውን ቅመማ ቅመም ይለውሱና ያዘጋጁ ነበር።

31. የቆሬያዊው የሰሎም በኵር ልጅ ሌዋዊው ማቲትያ የቍርባኑን እንጀራ የመጋገር ኀላፊነት ተሰጥቶት ነበር።

32. በየሰንበቱ ለሚዘጋጀው ገጸ ኅብስትም ኀላፊነቱ የተሰጠው ከቀዓታውያን ወንድሞቻቸው መካከል ለአንዳንዶቹ ነበር።

33. የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች የነበሩት መዘምራኑ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ክፍሎች ውስጥ እንዲኖሩና ከሌላው ሥራ ሁሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጎ ነበር፤ ምክንያቱም ቀንና ሌሊት የሚሠሩት ሥራ ነበራቸው።

34. እነዚህ ሁሉ የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች ሲሆኑ፣ በትውልድ ሐረጋቸው መሠረት ተመዘገቡ፤ የሚኖሩትም በኢየሩሳሌም ነበረ።

35. የገባዖን አባት ይዒኤል የሚኖረው በገባዖን ነበረ፤የሚስቱም ስም መዓካ ይባላል።

36. የበኵር ልጁ ዓብዶን ሲሆን፣ የእርሱም ተከታዮች ዱር፣ ቂስ፣ በኣል፣ ኔር፣ ናዳብ፣

37. ጌዶር፣ አሒዮ፣ ዛኩር፣ ሚቅሎት ነበሩ።

38. ሚቅሎት ሳምአን ወለደ፤ እነርሱም ከዘመዶቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ይኖሩ ነበር።

39. ኔር ቂስን ወለደ፤ ቂስ ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦል ዮናታን፣ ሜልኪሳን፣ አሚናዳብን፣ አስበኣልን ወለደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 9