ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 9:18-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. እርሱም በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በንጉሡ በር እስካሁን ድረስ ተመድቦአል። እነዚህም የሌዋውያኑ ሰፈር በር ጠባቂዎች ነበሩ።

19. የቆሬ ልጅ የአብያሳፍ ልጅ፣ የቆሬ ልጅ ሰሎምና ከእርሱም ቤተ ሰብ የሆኑት ቆሬያውያን ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚያስገባውን በር ይጠብቁ እንደ ነበር ሁሉ፣ እነዚህም ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባውን በር ይጠብቁ ነበር።

20. በቀድሞ ጊዜ የበር ጠባቂዎቹ አለቃ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።

21. ወደ መገናኛው ድንኳን የሚያስገባውን በር የሚጠብቀው ደግሞ የሜሱላም ልጅ ዘካርያስ ነበረ።

22. መግቢያ በሮቹን እንዲጠብቁ የተመረጡት ባጠቃላይ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ነበሩ። እነርሱም በትውልድ ሐረጋቸው መሠረት በሚኖሩባቸው መንደሮች ተቈጥረው ተመዘገቡ፤ በር ጠባቂዎቹን በዚያ ቦታ ላይ የመደቡአቸው ዳዊትና ባለ ራእዩ ሳሙኤል ነበሩ።

23. የማደሪያውን ድንኳን ማለትም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠብቁትም እነርሱና ዘሮቻቸው ነበሩ።

24. በር ጠባቂዎቹም በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜንና፣ በደቡብ በሚገኙት በአራቱም ማዕዘኖች ላይ ነበሩ።

25. ወንድሞቻቸውም በየመንደሮቻቸው ሆነው በየጊዜው እየወጡ የጥበቃውን ሥራ ሰባት ሰባት ቀን ያግዙአቸው ነበር።

26. ሌዋውያን የነበሩት አራቱ የበር ጠባቂ አለቆች ግን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሚገኙትን ክፍሎችና ግምጃ ቤቶች በኀላፊነት ይጠብቁ ነበር።

27. የጥበቃውን ሥራ የሚያከናውኑት እነርሱ በመሆናቸው የሚያድሩትም በዚያው በእግዚአብሔር ቤት አካባቢ ነበረ፤ ጠዋት ጠዋትም ደጆቹን የሚከፍቱት እነርሱ ነበሩ።

28. ከእነርሱም አንዳንዶቹ ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን በኀላፊነት ይጠብቁ ነበር፤ ዕቃዎቹም በሚገቡበትና በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ይቈጥሩ ነበር፤

29. ሌሎቹ ሌዋውያን ደግሞ ዕቃዎቹንና የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት፣ ዱቄቱን፣ የወይን ጠጁን፣ የወይራ ዘይቱን፣ ዕጣኑን፣ የሽቱውን ቅመማ ቅመም እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።

30. ከካህናቱም አንዳንዶቹ የሽቱውን ቅመማ ቅመም ይለውሱና ያዘጋጁ ነበር።

31. የቆሬያዊው የሰሎም በኵር ልጅ ሌዋዊው ማቲትያ የቍርባኑን እንጀራ የመጋገር ኀላፊነት ተሰጥቶት ነበር።

32. በየሰንበቱ ለሚዘጋጀው ገጸ ኅብስትም ኀላፊነቱ የተሰጠው ከቀዓታውያን ወንድሞቻቸው መካከል ለአንዳንዶቹ ነበር።

33. የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች የነበሩት መዘምራኑ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ክፍሎች ውስጥ እንዲኖሩና ከሌላው ሥራ ሁሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጎ ነበር፤ ምክንያቱም ቀንና ሌሊት የሚሠሩት ሥራ ነበራቸው።

34. እነዚህ ሁሉ የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች ሲሆኑ፣ በትውልድ ሐረጋቸው መሠረት ተመዘገቡ፤ የሚኖሩትም በኢየሩሳሌም ነበረ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 9