ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 29:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. እንዲሁም ለወርቁ ሥራ፣ ለብሩ ሥራ፣ በባለ ሙያዎች ለሚሠራው ሥራ ሁሉ የሚሆን ነው። ታዲያ ዛሬ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመቀደስ ፈቃደኛ የሚሆን ማን ነው?”

6. ከዚያም የቤተ ሰቡ መሪዎች፣ የነገዱ የእስራኤል ሹማምት፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም በንጉሡ ሥራ ላይ የተመደቡ ሹማምት በፈቃዳቸው ሰጡ፤

7. ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ የሰጡትም አምስት ሺህ መክሊት ወርቅ፣ ዐሥር ሺህ ዳሪክ ወርቅ፣ ዐሥር ሺህ መክሊት ብር፣ ዐሥራ ስምንት ሺህ መክሊት ናስ አንድ መቶ ሺህ መክሊት ብረት ነው።

8. የከበሩ ድንጋዮች ያለውም ሁሉ፣ በጌድሶናዊው በይሒኤል አማካይነት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አስገባ።

9. ስጦታው በገዛ ፈቃድና በፍጹም ልብ የቀረበ በመሆኑ፣ አለቆቹ ስላደረጉት የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሕዝቡ ደስ አለው፤ ንጉሥ ዳዊትም እንደዚሁ እጅግ ደስ አለው።

10. ዳዊትም በመላው ጉባኤ ፊት እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል አመሰገነ፤“የአባታችን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአንተ ምስጋና ይሁን።

11. እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይናበምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ።

12. ባለጠግነትና ክብር የሚገኘው ከአንተ ነው፤አንተም የሁሉ ገዢ ነህ፤ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለሁሉም ብርታትን ለመስጠት፣ብርታትና ኀይል በእጅህ ነው።

13. አምላካችን ሆይ፤ አሁንም እናመሰግንሃለን፤ለከበረው ስምህም ውዳሴ እናቀርባለን።

14. “ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፤ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ቸርነት እናድርግ ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው?

15. እኛም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን በፊትህ መጻተኞችና እንግዶች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፤ ተስፋ ቢስም ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 29