ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 29:2-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እኔም ያለኝን ሀብት ለአምላኬ ቤተ መቅደስ ለወርቁ ሥራ ወርቁን፣ ለብሩ ሥራ ብሩን፣ ለናሱ ሥራ ናሱን፣ ለብረቱ ሥራ ብረቱን፣ ለዕንጨቱ ሥራ ዕንጨቱን እንዲሁም ለፈርጥ የሚሆነውን መረግድ፣ ኬልቄዶን፣ ልዩ ልዩ ኅብር ያላቸውን የከበሩ ድንጋዮች፣ ማናቸውንም ዐይነት የሚያምር ድንጋይና ዕብነበረድ፣ ይህን ሁሉ በብዛት አዘጋጅቻለሁ።

3. ከዚህም በቀር ለአምላኬ ቤት ካለኝ ፍቅር የተነሣ ለዚህ ለተቀደሰ ቤት ከዚህ በፊት ከሰጠሁት በተጨማሪ ለዚሁ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የግል ሀብቴ የሆነውን ወርቅና ብር እሰጣለሁ፤

4. ይህም ሦስት ሺህ መክሊት የኦፊር ወርቅና ሰባት ሺህ መክሊት ንጹሕ ብር ለቤተ መቅደሱ የግድግዳ ግንብ ማስጌጫ

5. እንዲሁም ለወርቁ ሥራ፣ ለብሩ ሥራ፣ በባለ ሙያዎች ለሚሠራው ሥራ ሁሉ የሚሆን ነው። ታዲያ ዛሬ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመቀደስ ፈቃደኛ የሚሆን ማን ነው?”

6. ከዚያም የቤተ ሰቡ መሪዎች፣ የነገዱ የእስራኤል ሹማምት፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም በንጉሡ ሥራ ላይ የተመደቡ ሹማምት በፈቃዳቸው ሰጡ፤

7. ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ የሰጡትም አምስት ሺህ መክሊት ወርቅ፣ ዐሥር ሺህ ዳሪክ ወርቅ፣ ዐሥር ሺህ መክሊት ብር፣ ዐሥራ ስምንት ሺህ መክሊት ናስ አንድ መቶ ሺህ መክሊት ብረት ነው።

8. የከበሩ ድንጋዮች ያለውም ሁሉ፣ በጌድሶናዊው በይሒኤል አማካይነት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አስገባ።

9. ስጦታው በገዛ ፈቃድና በፍጹም ልብ የቀረበ በመሆኑ፣ አለቆቹ ስላደረጉት የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሕዝቡ ደስ አለው፤ ንጉሥ ዳዊትም እንደዚሁ እጅግ ደስ አለው።

10. ዳዊትም በመላው ጉባኤ ፊት እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል አመሰገነ፤“የአባታችን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአንተ ምስጋና ይሁን።

11. እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይናበምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ።

12. ባለጠግነትና ክብር የሚገኘው ከአንተ ነው፤አንተም የሁሉ ገዢ ነህ፤ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለሁሉም ብርታትን ለመስጠት፣ብርታትና ኀይል በእጅህ ነው።

13. አምላካችን ሆይ፤ አሁንም እናመሰግንሃለን፤ለከበረው ስምህም ውዳሴ እናቀርባለን።

14. “ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፤ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ቸርነት እናድርግ ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው?

15. እኛም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን በፊትህ መጻተኞችና እንግዶች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፤ ተስፋ ቢስም ነው።

16. እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ለተቀደሰው ስምህ ቤተ መቅደስ እንሠራልህ ዘንድ ይህ በብዛት ያዘጋጀነው ሁሉ፣ ከእጅህ የተገኘና ሁሉም የአንተ ነው።

17. አምላኬ ሆይ፤ ልብን እንደምትመረምርና ቅንነትን እንደምትወድ ዐውቃለሁ፤ እኔም ይህን ሁሉ የሰጠሁት በበጎ ፈቃድና በቀና መንፈስ ነው። አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በበጎ ፈቃዱ እንዴት እንደ ሰጠ አይቻለሁ።

18. የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን ዐሳብ ለዘላለም በሕዝብህ ልብ ጠብቀው፤ ልባቸውንም ለአንተ ታማኝ አድርገው።

19. ትእዛዞችህን፣ ደንብህንና ሥርዐትህን እንዲጠብቅ፣ እኔ ባዘጋጀሁለት ነገሮች ታላቅ ሕንጻ ለመሥራት እንዲችል፣ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ፈቃደኝነት ስጠው።

20. ከዚያም ዳዊት ለመላው ጉባኤ፣ “አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱት” አላቸው። ስለዚህ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ወደሱ፤ በእግዚአብሔር በንጉሡም ፊት ተደፍተው ሰገዱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 29