ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከአሞናውያን ጋር የተደረገ ጦርነት

1. ከዚህ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ ሞተ፤ ልጁም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

2. ዳዊትም፣ “አባቱ ለእኔ በጎ ነገር እንዳደረገልኝ እስቲ እኔም ለናዖስ ልጅ ለሐኖን በጎ ነገር ላድርግለት” ብሎ አሰበ። ስለዚህ ዳዊት ስለ አባቱ ሞት ሐዘኑን ለመግለጽ ወደ ሐኖን መልክተኞችን ላከ። የዳዊት ሰዎች ሐዘናቸውን ለመግለጽ ሐኖን ወደሚኖርበት ወደ አሞናውያን ምድር በመጡ ጊዜ፣

3. የአሞናውያን መኳንንት ለሐኖን “ዳዊት ሐዘኑን ለመግለጽ ሰዎችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃልን? ሰዎቹ ወደ አንተ የመጡት አገሪቱን ለመመርመር፣ ለመሰለልና ለመያዝ አይደለምን?” አሉት።

4. ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ ላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ መኻል ለመኻል ቀዶ ሰደዳቸው።

5. በሰዎቹ ላይ የደረሰባቸውን ዳዊት በሰማ ጊዜ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር፣ ወደ እነርሱ መልክተኞችን ላከ፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ትመጣለችሁ” አለ።

6. አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባወቁ ጊዜ፣ ሐኖንና አሞናውያን ከመስጴጦምያ፣ ከአራም መዓካና ከሱባ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመከራየት አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ፤

7. ከዚያም ሠላሳ ሁለት ሺህ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን እንዲሁም የመዓካን ንጉሥና ወታደሮች በገንዘብ ቀጠሩ፤ እነርሱም መጥተው በሜድባ አጠገብ ሲሰፍሩ፣ አሞናውያን ደግሞ ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ለጦርነት ወጡ።

8. ዳዊት ይህን ሲሰማ ኢዮአብንና መላውን ተዋጊ ሰራዊት ላከ።

9. አሞናውያንም መጥተው ወደ ከተማቸው በሚያስገባው በር ላይ ለጦርነት ተሰለፉ፤ የመጡት ነገሥታት ደግሞ ብቻቸውን በሜዳው ላይ ነበሩ።

10. ኢዮአብም ከፊቱና ከኋላው ጦር መኖሩን አየ፤ ስለዚህ በእስራኤል የታወቁትን ጀግኖች መርጦ ሶርያውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።

11. የቀሩትም ሰዎች በወንድሙ በአቢሳ ሥር ሆነው አሞናውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።

12. ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ “ሶርያውያን ከበረቱብኝ አንተ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን ከበረቱብህ ደግሞ እኔ እረዳሃለሁ።

13. እንግዲህ በርቱ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችን ከተሞች ብለን በጀግንነት እንዋጋ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ።”

14. ከዚያም ኢዮአብና አብረውት ያሉት ወታደሮች ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሡ፤ ሶርያውያንም ከፊታቸው ሸሹ።

15. አሞናውያንም ሶርያውያን መሸሻቸውን ሲያዩ፣ እነርሱም ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

16. ሶርያውያን በእስራኤል መሸነፋቸውን ሲያዩ፣ መልክተኞችን ልከው ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጡ፤ እነዚህንም የሚመራቸው የአድርአዛር ሰራዊት አዛዥ ሾፋክ ነበረ።

17. ዳዊት ይህን ሲሰማ፣ እስራኤልን ሁሉ ሰብስቦ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ወደ ፊት በመገሥገሥም ከፊት ለፊታቸው የውጊያ መሥመሩን ያዘ። ዳዊትም ሶርያውያንን ጦርነት ለመግጠም ወታደሮቹን አሰለፈ፤ እነርሱም ተዋጉት።

18. ይሁን እንጂ ከእስራኤል ፊት ሸሹ። ዳዊትም ሰባት ሺህ ሠረገለኞችና አርባ ሺህ እግረኛ ወታደሮች ገደለ። የሠራዊታቸው አዛዥ ሾፋክም በጦርነቱ ላይ ሞተ።

19. የአድርአዛርም ሹማምት በእስራኤል መሸነፋቸውን ሲያዩ፣ ከዳዊት ጋር ታረቁ፤ ገባሮቹም ሆኑ።ስለዚህ ሶርያውያን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አሞናውያንን ለመርዳት ፈቃደኞች አልሆኑም።