ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳዊት የተቀዳጃቸው ድሎች

1. ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል መትቶ ተገዥ አደረጋቸው፤ ጌትንና በዙሪያዋም የሚገኙትን መንደሮች ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወሰደ።

2. እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረጋቸው፤ እነርሱም ገባሮቹ ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት።

3. ከዚህም በላይ ዳዊት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመቈጣጠር በሄደ ጊዜ፣ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሐማት ድረስ ዘልቆ ወጋው።

4. ዳዊትም አንድ ሺህ ሠረገላ፣ ሰባት ሺህ ፈረሰኛና ሃያ ሺህ እግረኛ ወታደር ማረከ፤ አንድ መቶ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ አስቀርቶ የቀሩትን ቋንጃቸውን ቈረጠ።

5. ሶርያውያንም የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት ከደማስቆ በመጡ ጊዜ፣ ከእነርሱ ሃያ ሁለት ሺህ ሰው ገደለ።

6. ከዚያም በሶርያ ግዛት ውስጥ ባለችው በደማስቆ የጦር ሰፈር አቋቋመ፤ ሶርያውያን ገባሮቹ ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አጐናጸፈው።

7. ዳዊትም የአድርአዛር ጦር አለቆች ያነገቡትን የወርቅ ጋሻ ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣው።

8. ዳዊት ከአድርአዛር ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ሰሎሞን የናሱን ባሕር፣ ዐምዶቹንና ልዩ ልዩ የናስ ዕቃዎቹን የሠራው በዚሁ ነበር።

9. የሐማት ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ሰራዊት ሁሉ ድል እንደመታ ሲሰማ፣

10. እጅ እንዲነሣውና ደስታውንም እንዲገልጥለት ልጁን አዳራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ ቶዑ ከአድርአዛር ጋር ብዙ ጊዜ ጦርነት ገጥሞ ነበር። አዶራምም ከወርቅ፣ ከብርና ከናስ የተሠሩ ልዩ ልዩ ዕቃዎች አመጣለት።

11. ንጉሥ ዳዊት ከኤዶም፣ ከሞዓብ፣ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጥኤማውያንና ከአማሌቃውያን ከእነዚህ ሁሉ መንግሥታት የማረከውን ወርቅና ብር ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህንም ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ቀደሰ።

12. የጽሩያ ልጅ አቢሳ በጨው ሸለቆ ዐሥራ ስምንት ሺህ ኤዶማውያን ገደለ።

13. እርሱም በኤዶም የጦር ሰፈሮች አቋቋመ፤ ኤዶማውያንም ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አጐናጸፈው።

የዳዊት ሹማምት

14. ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍትሕንና ጽድቅን አሰፈነላቸው።

15. የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የሰራዊቱ አዛዥ ነበረ፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ደግሞ የቤተ መዛግብቱ ኀላፊ ነበረ።

16. የአኪጦብ ልጅ ሳዶቅና የአቤሜሌክ ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ደግሞ ጸሓፊ ነበረ።

17. የዮዳሄ ልጅ በናያስ የከሊታውያንና የፈሊታውያን አዛዥ ነበረ። የዳዊት ወንዶች ልጆቹ ደግሞ ከንጉሡ ቀጥሎ የበላይ ሹማምት ነበሩ።