ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 17:4-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. “ሂድና ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ እኔ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም።

5. እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ከአንዱ ድንኳን ወደ ሌላው ድንኳን፣ ከአንዱ ማደሪያ ወደ ሌላው ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ፣ በቤት ውስጥ አልኖርሁም።

6. ከእስራኤላውያን ጋር በሄድሁባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሕዝቤን እንዲጠብቁ ላዘዝኋቸው መሪዎቻቸው ከቶ፣ “ለምን ከዝግባ ዕንጨት ቤት አልሠራችሁልኝም ያልሁበት ጊዜ አለን?”

7. “እንግዲህ አሁንም ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘የሕዝቤ የእስራኤል ገዥ እንድትሆን በጎችን ከመጠበቅና ከመከተል አንሥቼ ወሰድሁህ።

8. በሄድህበት ሁሉ ከአንተ አልተለየሁም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስምህን እንደ ምድር ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።

9. ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጠዋለሁ፤ የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው ከእንግዲህም በኋላ እንዳይናወጡ አደርጋቸዋለሁ። ክፉ ሰዎች በመጀመሪያ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ከእንግዲህ አይጨቁኗቸውም፤

10. ከዚህ ቀደም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪዎች በሾምሁ ጊዜ ጨቋኞቹ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉትም፤ ጠላቶቻችሁን ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ።“ ‘እግዚአብሔር ቤት እንደሚሠራልህ በግልጽ እነግርሃለሁ፤

11. ዘመንህን ጨርሰህ ወደ አባቶችህ በምትሄድበት ጊዜ፣ ከአብራክህ ከተከፈሉት ልጆችህ አንዱ በእግርህ እንዲተካ አደርጋለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለታለሁ፤

12. ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ።

13. አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደወሰድሁ፣ ከእርሱ ላይ ከቶ አልወስድም።

14. በቤቴና በመንግሥቴ ላይ ለዘላለም አኖረዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል።” ’

15. ናታንም የዚህን ሁሉ ራእይ ቃል ለዳዊት ነገረው።

16. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦም እንዲህ አለ፤“እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለመሆኑ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤስ ምንድን ነው?

17. አምላክ ሆይ፤ ይህ በፊትህ በቂ እንዳልሆነ ቈጥረህ ስለ ወደፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ እኔንም ከሰዎች ሁሉ እጅግ የከበረ ሰው አድርገህ ተመለከትኸኝ።

18. “ባሪያህን ስላከበርኸው፣ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ማለት ይችላል? ባሪያህን እኮ ታውቀዋለህ፤

19. እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ።

20. “አቤቱ፤ እንደ አንተ ያለ የለም፤ በጆሮአችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 17