ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የዳዊት ቤትና ቤተ ሰቡ

1. በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት ቤተ መንግሥት እንዲሠሩ መልክተኞችን፣ ድንጋይ ጠራቢዎችንና አናጢዎችን ከዝግባ ዕንጨት ጋር ላከ።

2. ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ አንግሦ እንዳጸናውና ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል ሲል መንግሥቱን ከፍ ከፍ እንዳደረገለት አስተዋለ።

3. ዳዊትም በኢየሩሳሌም ብዙ ሚስቶች አገባ፤ ከእነርሱም ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ።

4. በዚያ ሳለ የወለዳቸው የልጆቹ ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣

5. ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ኤሊፋላት፣

6. ኖጋ፣ ናፌቅ፣ ያፍያ፣

7. ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት።

ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረገ

8. ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ተቀብቶ መንገሡን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ፍለጋ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊት ይህን ሰምቶ ስለ ነበር ሊገጥማቸው ወጣ።

9. በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው የራፋይምን ሸለቆ ወረሩ።

10. ስለዚህ ዳዊት፣ “ወጥቼ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ልጣልን? አንተስ በእጄ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ውጣ! በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ” ብሎ መለሰለት።

11. ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ በኣልፐራሲም ወጡ፤ በዚያም ድል አደረጋቸው። ዳዊትም፣“ውሃ ነድሎ እንደሚወጣ ሁሉ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው” አለ፤ ከዚህም የተነሣ ያን ቦታ “በኣልፐራሲም” ብለው ሰየሙት።

12. ፍልስጥኤማውያን አማልክቶቻቸውን በዚያው ጥለዋቸው ስለ ነበር፣ ዳዊት በእሳት እንዲያቃጥሏቸው አዘዘ።

13. ፍልስጥኤማውያን ሸለቆውን እንደ ገና ወረሩ፤

14. ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት “ዙሪያውን ከበህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት አደጋ ጣልባቸው እንጂ በቀጥታ ወደ ላይ አትውጣ፤

15. በሾላው ዐናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ወዲያውኑ ለጦርነት ውጣ፤ ይህም የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቶአል ማለት ነውና።”

16. ስለዚህ ዳዊት እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ ከገባዖን ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መቷቸው።

17. ከዚህም የተነሣ የዳዊት ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ እግዚአብሔርም መንግሥታት ሁሉ እንዲፈሩት አደረገ።