ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 13:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዳዊትም ሻለቆችና መቶ አለቆች ከሆኑት የጦር ሹማምቱ ሁሉ ጋር ተማከረ።

2. ከዚያም ለመላው የእስራኤል ማኅበር እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ነገሩ መልካም መስሎ ከታያችሁና የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፣ በእስራኤል ግዛት ሁሉ ለሚኖሩ በሩቅም ሆነ በቅርብ ላሉት ለቀሩት ወንድሞቻችን እንዲሁም በየራሳቸው ከተሞችና መሰማሪያዎች የሚኖሩ ካህናትና ሌዋውያን መጥተው ከእኛ ጋር እንዲሰባሰቡ እንላክባቸው።

3. በሳኦል ዘመነ መንግሥት ሳንፈልገው የነበረውን የአምላካችንን ታቦት መልሰን ወደ እኛ እናምጣ”።

4. ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ መላው ማኅበር ይህንኑ ለማድረግ ተስማማ።

5. ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከቂርያትይዓሪም ለማምጣት ከግብፅ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ሐማት መተላለፊያ ድረስ የሰፈሩትን እስራኤላውያን ሁሉ ሰበሰበ።

6. ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን፣ የእግዚአብሔር አምላክን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም ወደተባለችው ወደ በኣላ ሄዱ።

7. የእግዚአብሔርንም ታቦት ከአሚናዳብ ቤት በአዲስ ሠረገላ ላይ አድርገው አመጡት፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም ዖዛና አሒዮ ነበሩ።

8. ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሆነው በቅኔና በበገና፣ በመሰንቆና በከበሮ፣ በጸናጽልና በመለከት በሙሉ ኀይላቸው በዓሉን በደስታ ያከብሩ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 13