ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 10:6-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ስለዚህ ሳዖልና ሦስት ልጆቹ ሞቱ፤ ቤተ ሰዎቹም ሁሉ አብረው ሞቱ።

7. በሸለቆው ውስጥ የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ሰራዊቱ እንደ ሸሸ፣ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ከተሞቹን ያዙ።

8. በማግሥቱ ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ ሲመጡ፣ ሳኦልና ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው።

9. ሳኦልን ከገፈፉ፣ ራሱን ከቈረጡና መሣሪያውንም ከወሰዱ በኋላ፣ ለአማልክቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራቹን እንዲነግሩ ወደ መላው የፍልስጥኤም ምድር መልክተኞችን ላኩ።

10. ከዚያም መሣሪያውን በአማልክቶቻቸው ቤተ ጣዖት አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤተ ጣዖት ውስጥ አንጠለጠሉት።

11. የኢያቢስ ገለዓድ ነዋሪዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን በሰሙ ጊዜ፣

12. ብርቱ የሆኑ ሰዎች ሄደው የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ አንሥተው ወደ ኢያቢስ አመጡ፤ ዐጽማቸውንም ኢያቢስ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤ ከዚያም ሰባት ቀን ጾሙ።

13. ሳኦል እግዚአብሔርን ስላልታዘዘ ሞተ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልጠበቀም፤ ይልቁንም ከሙታን ጠሪ ምክርን ጠየቀ፤

14. ይህን ከእግዚአብሔር አልጠየቀም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት እንዲተላለፍ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 10