ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 9:11-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ንጉሥ ሰሎሞን በገሊላ የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ለጢሮስ ንጉሥ ለኪራም ሰጠው፤ ንጉሡ ይህን ያደረገውም፣ የሚያስፈልገውን ሁሉ ዝግባ፣ ጥድና ወርቅ ኪራም ሰጥቶት ስለ ነበር ነው፤

12. ይሁን እንጂ ኪራም ከጢሮስ ተነሥቶ ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ለማየት በሄደ ጊዜ አልተደሰተባቸውም፤

13. እርሱም፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ ከተሞች ምንድን ናቸው?” አለ፤ እነዚህንም ‘ከቡል ምድር’ አላቸው፤ እስከ ዛሬም በዚሁ ስም ይጠራሉ።

14. በዚያን ጊዜ ኪራም ለንጉሡ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ልኮለት ነበር።

15. ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ የራሱን ቤተ መንግሥት፣ ሚሎን፣ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ሐጾርን፣ መጊዶንና ጌዝርን ለመሥራት የጒልበት ሠራተኞች መልምሎ ነበር።

16. የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ በጌዝር ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ አቃጠላትም፤ ነዋሪዎቿን ከነዓናውያንን ገድሎ ለልጁ ለሰሎሞን ሚስት መዳሪያ አድርጎ ሰጥቶአት ነበር፤

17. ሰሎሞንም ጌዝርን መልሶ ሠራት፤ እንዲሁም የታችኛውን ቤትሖሮንን፣

18. ባዕላትን፣ በይሁዳ ምድር በምድረ በዳው የምትገኘውን ተድሞርን ሠራ፤

19. ደግሞም ማናቸውንም በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በሌሎች ግዛቶቹ ሁሉ ለመሥራት የፈለገውን፣ ሥንቅ የሚከማችባቸውን፣ ሠረገሎች የሚጠበቁባቸውን እንዲሁም ፈረሰኞች የሚቀመጡባቸውን ከተሞችና መንደሮች ሁሉ ሠራ።

20. ከእስራኤል ሕዝብ ያልሆኑትን ከአሞራውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤውያውንና ከኢያቡሳውያን ሕዝቦች ሁሉ የተረፉትን፣

21. እስራኤላውያን ዘሮቻቸውን ለማጥፋት ያልቻሉትንና በምድሪቱ የቀሩትን እነዚህን እስከ ዛሬ እንደሚደረገው ሁሉ፣ ሰሎሞን ለግዳጅ ሥራ መለመላቸው።

22. ይሁን እንጂ ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ወታደሮቹ፣ ሹማምቱ፣ የጦር አለቆቹ፣ ሻምበሎቹ፣ ባልደራሶቹ ነበሩ።

23. እነዚህም ሰሎሞን የሚያሠራውን የሕንጻ ሥራ የሚያከናውኑትን ሠራተኞች የሚቈጣጠሩ ናቸው፤ ቍጥራቸውም አምስት መቶ አምሳ ነበር።

24. የፈርዖን ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወዳሠራላት ቤተ መንግሥት ከመጣች በኋላ ሰሎሞን ሚሎንን ሠራ።

25. ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ባሠራው መሠዊያ ላይ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በማቅረብ፣ ከዚሁ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም የቤተ መቅደሱን ግዳጅ ተወጣ።

26. እንዲሁም ንጉሡ ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር፣ በኤሎት አጠገብ፣ በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 9