ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 7:8-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ከአዳራሹ በስተ ጀርባ ባለው አደባባይ መኖሪያው እንዲሆን የተሠራው ቤተ መንግሥትም የዚሁ ተመሳሳይ ነበር። ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ይህንኑ ቤተ መንግሥት የመሰለ አዳራሽ ሠራ።

9. ከውጭ አንሥቶ እስከ ትልቁ አደባባይ፣ ከመሠረቱ አንሥቶ እስከ ድምድማቱ ያለው የሕንጻ ሥራ በሙሉ፣ በውስጥም በውጭም በልክ በልኩ በተቈረጠና አምሮ በተስተካከለ ምርጥ ድንጋይ የተሠራ ነበር።

10. መሠረቱም ዐሥርና ስምንት ክንድ ርዝመት ባላቸውና ምርጥ በሆኑ ታላላቅ ድንጋዮች የተሠራ ነበር።

11. በላዩም ላይ ምርጥ የሆኑ፣ በልክ በልኩ የተቈረጡ ድንጋዮችና የዝግባ ሳንቃዎች ነበሩ።

12. የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ከመመላለሻ በረንዳው ጭምር እንደ ትልቁ አደባባይ አምሮ በተጠረበ ሦስት ረድፍ ድንጋይና ተስተካክሎ በተከረከመ በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ የታጠረ ነበር።

13. ንጉሥ ሰሎሞንም መልእክተኛ ልኮ ኪራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ አስመጣ፤

14. የኪራም እናት ከንፍታሌም ነገድ ስትሆን፣ እርሷም መበለት ነበረች፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን፣ የናስ ሥራ ባለ ሙያ ነበር። ኪራም በማናቸውም የናስ ሥራ ጥበብን፣ ማስተዋልንና ዕውቀትን የተሞላ ሰው ነበር፤ እርሱም ወደ ንጉሥ ሰሎሞን መጥቶ የተመደበለትን ሥራ ሁሉ አከናወነ።

15. ኪራም የእያንዳንዱ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ፣ ዙሪያው ዐሥራ ሁለት ክንድ የሆነ፣ ሁለት የናስ ምሰሶዎች ሠራ።

16. እንዲሁም በምሰሶዎቹ አናት ላይ የሚሆኑ፣ ሁለት ጒልላት ከቀለጠ ናስ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ጒልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበር።

17. በምሰሶዎቹ አናት ላይ ላሉት ጒልላቶችም ጌጥ እንዲሆኑ፣ ለእያንዳንዳቸው ሰባት የመረብ ሰንሰለት አበጀ፤

18. ደግሞም በምሰሶዎቹ ላይ ያሉትን ጒልላቶች ለማስጌጥ የእያንዳንዱን መረብ ዙሪያ የሚከቡ ሮማኖች በሁለት ረድፍ ሠራ፤ ለሁለቱም ጒልላቶች ያደረገው ተመሳሳይ ነበር።

19. በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጒልላቶች ቁመታቸው አራት ክንድ ሲሆን፣ የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው።

20. በሁለቱም የምሰሶ ጒልላቶችና ከመርበቡ ቀጥሎ ባለው የክብ ቅርጽ ላይ ዙሪያውን በሙሉ ሁለት መቶ ሮማኖች በተርታ ነበሩ።

21. ምሰሶዎቹንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ላይ አቆመ፤ በስተ ደቡብ ያቆመውን ምሰሶ ያቁም፣ በስተ ሰሜን በኩል ያለውንም ቦዔዝ ብሎ ጠራው።

22. አናቱ ላይ ያሉት ጒልላቶች የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ሁኔታ ተፈጸመ።

23. ቅርጹ ክብ፣ ስፋቱ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፣ ቁመቱ አምስት ክንድ የሆነ ክብ ገንዳ ከቀለጠ ብረት ሠራ፤ ዙሪያውም ሲለካ ሠላሳ ክንድ ሆነ።

24. ከከንፈሩም ዝቅ ብሎ፣ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ እንደ ቅል ያሉ ዐሥር ቅርጾች ዙሪያውን በሁለት ረድፍ ከበውታል፤ እነዚህም ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ተሠርተው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 7