ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 7:6-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሰሎሞን፣ “ባለ ብዙ ምሰሶ አዳራሽ” የተባለ ቤት ሠራ፤ የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሠላሳ ክንድ፣ ነበር፤ በስተ ፊት በኩልም ጣራ ያለውና በአዕማድ የተደገፈ መመላለሻ ነበረው።

7. ዳኝነት የሚያይበትንም የዙፋን ችሎት አዳራሽ ሠራ፤ ይኸውም የፍትሕ አዳራሽ የተባለው ነው፤ ይህንንም ከወለሉ አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃ ሸፈነው።

8. ከአዳራሹ በስተ ጀርባ ባለው አደባባይ መኖሪያው እንዲሆን የተሠራው ቤተ መንግሥትም የዚሁ ተመሳሳይ ነበር። ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ይህንኑ ቤተ መንግሥት የመሰለ አዳራሽ ሠራ።

9. ከውጭ አንሥቶ እስከ ትልቁ አደባባይ፣ ከመሠረቱ አንሥቶ እስከ ድምድማቱ ያለው የሕንጻ ሥራ በሙሉ፣ በውስጥም በውጭም በልክ በልኩ በተቈረጠና አምሮ በተስተካከለ ምርጥ ድንጋይ የተሠራ ነበር።

10. መሠረቱም ዐሥርና ስምንት ክንድ ርዝመት ባላቸውና ምርጥ በሆኑ ታላላቅ ድንጋዮች የተሠራ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 7