ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 7:24-42 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. ከከንፈሩም ዝቅ ብሎ፣ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ እንደ ቅል ያሉ ዐሥር ቅርጾች ዙሪያውን በሁለት ረድፍ ከበውታል፤ እነዚህም ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ተሠርተው ነበር።

25. ገንዳውም፣ ሦስቱ ፊታቸውን ወደ ሰሜን፣ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ባዞሩ የዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስሎች ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ገንዳው በላያቸው ሆኖ የሁሉም የኋላ አካል በመካከል ላይ የገጠመ ነበር።

26. የገንዳው ውፍረት አንድ ጋት ሲሆን፣ የከንፈሩ ጠርዝ ደግሞ እንደ አበባ ቅርጽ ሆኖ፣ የጽዋ ከንፈር የመሰለ ነው፤ ይህም አርባ ሁለት ሺህ ሊትር ያህል ውሃ የሚይዝ ነበር።

27. እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ዐሥር ባለ መንኰራኵር የዕቃ ማስቀመጫዎች ከመዳብ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ርዝመት አራት ክንድ፣ ወርድ አራት ክንድ፣ ቁመትም ሦስት ክንድ ነበር።

28. የዕቃ ማስቀመጫዎቹ የተሠሩት እንደዚህ ነው፤ እነዚህም ቀጥ ብለው ከቆሙ ደጋፊዎች ጋር የተያያዙ ባለ አራት ማእዘን ጠፍጣፋ ናሶች ነበሯቸው።

29. ዳርና ዳር ባሉት ድጋፎች መካከል በሚገኙት ጠፍጣፋ ናሶች ላይ የአንበሶችን፣ የኮርማዎችንና የኪሩቤልን ምስል አደረገ፤ በድጋፎቹም ላይ እንደዚሁ አደረገ። ከአንበሶቹና ከኮርማዎቹ በላይና በታች በኩል ደግሞ የአበባ ጒንጒን የሚመስሉ ተቀጥቅጠው የተሠሩ ቅርጾች ነበሩ።

30. እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት የናስ መንኰራኵርና መንኰራኵሮቹ የሚሽከረከሩባቸው የናስ ወስከምቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው በአራቱም ማእዘን ገጽ ላይ የአበባ ጒንጒን ቀልጦ የተሠራባቸው የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበረው።

31. በዕቃ ማስቀመጫወቹም ውስጥ ጥልቀቱ አንድ ክንድ የሆነ ባለ ክብ ክፍተት ነበር፤ ይህም ክፍተት ድቡልቡል ሆኖ ከታች ከመቆሚያው በኩል ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ወርድ ሲኖረው፣ በክፍተቱም ዙሪያ ቅርጾች ነበሩ፤ ክፈፎቹ ግን ባለ አራት ማእዘን እንጂ ክብ አልነበሩም።

32. አራቱ መንኰራኵሮች በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ናስ ሥር ሲሆኑ፣ የመንኰራኵሮቹ ወስከምቶች ደግሞ ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር የተያያዙ ነበሩ፤ የእያንዳንዱም መንኰራኵር ስፋት አንድ ክንድ ተኩል ነበር።

33. መንኰራኵሮቹ የሠረገላ መንኰራኵር መሰል ሲሆኑ፣ ወስከምቶቹ የመንኮራኵሮቹ ክፈፎችና ዐቃፊዎቻቸው እንዲሁም ወስከምቶቹ የሚገቡባቸው ቧምቧዎች በሙሉ ከቀለጠ ብረት የተሠሩ ነበሩ።

34. እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ወጣ ያለ እጀታ ነበረው።

35. በዕቃ ማስቀመጫው ጫፍ ላይ ግማሽ ክንድ የሆነ ዙሪያ ክብ ነበረበት፤ ድጋፎቹና ጠፍጣፋ ናሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው አናት ጋር የተያያዙ ነበሩ።

36. እርሱም በድጋፎቹና በጠፍጣፋ ናሶቹ ላይ ባለው ቦታ ሁሉ፣ ዙሪያውን የአበባ ጒንጒን እያደረገ ኪሩቤልን፣ አንበሶችንና የዘንባባ ዛፎችን ቀረጸ።

37. ዐሥሩም የዕቃ ተሸካሚዎች የተሠሩት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ሁሉም ከአንድ ቅርጽ ቀልጠው የወጡ ስለ ሆነ፣ በመጠንና በቅርጽ ፍጹም ተመሳሳይ ነበሩ።

38. ከዚያም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ የሚሆን፣ እያንዳንዱ ስምንት መቶ ሰማንያ ሊትር የሚይዝ ዐሥር የናስ መታጠቢያ ገንዳ ሠራ፤ ስፋቱም አራት ክንድ ነበር።

39. ከዕቃ ማስቀመጫዎቹም አምስቱን ከመቅደሱ በስተ ደቡብ፣ አምስቱን በስተ ሰሜን በኩል አኖረ፤ ገንዳውንም ከቤተ መቅደሱ በደቡብ ምሥራቅ ጫፍ ላይ በስተ ደቡብ አኖረው።

40. እንዲሁም ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችንና ድስቶችን ሠራ፤ኪራምም በዚህ ሁኔታ ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንደሚከተለው ፈጸመ፤

41. ሁለቱን ምሰሶዎች፣በምሰሶዎቹ አናት ላይ በክብ ቅርጽ የተሠሩ ሁለት ጒልላቶችን፤በምሰሶዎቹ ላይ ያሉትን በክብ ቅርጽ የተሠሩትን ሁለት ጒልላት ያስጌጡትን ሁለት መረቦች፤

42. በምሰሶዎቹ አናት ላይ ያሉትንና ክብ ቅርጽ የያዙትን፣ በሁለት ረድፍ የተቀረጹትን መረቦች፣ የሚያስጌጡትን አራት መቶ ሮማኖች፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 7