ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 7:19-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጒልላቶች ቁመታቸው አራት ክንድ ሲሆን፣ የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው።

20. በሁለቱም የምሰሶ ጒልላቶችና ከመርበቡ ቀጥሎ ባለው የክብ ቅርጽ ላይ ዙሪያውን በሙሉ ሁለት መቶ ሮማኖች በተርታ ነበሩ።

21. ምሰሶዎቹንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ላይ አቆመ፤ በስተ ደቡብ ያቆመውን ምሰሶ ያቁም፣ በስተ ሰሜን በኩል ያለውንም ቦዔዝ ብሎ ጠራው።

22. አናቱ ላይ ያሉት ጒልላቶች የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ሁኔታ ተፈጸመ።

23. ቅርጹ ክብ፣ ስፋቱ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፣ ቁመቱ አምስት ክንድ የሆነ ክብ ገንዳ ከቀለጠ ብረት ሠራ፤ ዙሪያውም ሲለካ ሠላሳ ክንድ ሆነ።

24. ከከንፈሩም ዝቅ ብሎ፣ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ እንደ ቅል ያሉ ዐሥር ቅርጾች ዙሪያውን በሁለት ረድፍ ከበውታል፤ እነዚህም ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ተሠርተው ነበር።

25. ገንዳውም፣ ሦስቱ ፊታቸውን ወደ ሰሜን፣ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ባዞሩ የዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስሎች ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ገንዳው በላያቸው ሆኖ የሁሉም የኋላ አካል በመካከል ላይ የገጠመ ነበር።

26. የገንዳው ውፍረት አንድ ጋት ሲሆን፣ የከንፈሩ ጠርዝ ደግሞ እንደ አበባ ቅርጽ ሆኖ፣ የጽዋ ከንፈር የመሰለ ነው፤ ይህም አርባ ሁለት ሺህ ሊትር ያህል ውሃ የሚይዝ ነበር።

27. እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ዐሥር ባለ መንኰራኵር የዕቃ ማስቀመጫዎች ከመዳብ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ርዝመት አራት ክንድ፣ ወርድ አራት ክንድ፣ ቁመትም ሦስት ክንድ ነበር።

28. የዕቃ ማስቀመጫዎቹ የተሠሩት እንደዚህ ነው፤ እነዚህም ቀጥ ብለው ከቆሙ ደጋፊዎች ጋር የተያያዙ ባለ አራት ማእዘን ጠፍጣፋ ናሶች ነበሯቸው።

29. ዳርና ዳር ባሉት ድጋፎች መካከል በሚገኙት ጠፍጣፋ ናሶች ላይ የአንበሶችን፣ የኮርማዎችንና የኪሩቤልን ምስል አደረገ፤ በድጋፎቹም ላይ እንደዚሁ አደረገ። ከአንበሶቹና ከኮርማዎቹ በላይና በታች በኩል ደግሞ የአበባ ጒንጒን የሚመስሉ ተቀጥቅጠው የተሠሩ ቅርጾች ነበሩ።

30. እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት የናስ መንኰራኵርና መንኰራኵሮቹ የሚሽከረከሩባቸው የናስ ወስከምቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው በአራቱም ማእዘን ገጽ ላይ የአበባ ጒንጒን ቀልጦ የተሠራባቸው የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበረው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 7