ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 6:22-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ስለዚህ ውስጡን በሙሉ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ያለውን መሠዊያም እንደዚሁ በወርቅ ለበጠው።

23. በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ሁለት የኪሩቤል ቅርጽ ከወይራ ዕንጨት ሠራ፤

24. የአንደኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን፣ ሌላውም ክንፉ እንደዚሁ አምስት ክንድ ነበር፤ ይህም ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ዐሥር ክንድ ማለት ነው።

25. የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ እንደዚሁ ዐሥር ክንድ ሆነ፣ ሁለቱ ኪሩቤል በመጠንና በቅርጽ አንድ ዐይነት ነበሩና።

26. የእያንዳንዱም ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበር።

27. ክንፎቻቸው እንደ ተዘረጋ፣ ኪሩቤልን ወስዶ በቅድስተ ቅዱሳኑ አኖራቸው፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አንዱን ግድግዳ ሲነካ፣ የሌላው ኪሩብ ክንፍ ደግሞ ሌላውን ግድግዳ ይነካ ነበር፤ ሌሎቹ ክንፎቻቸውም በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር።

28. ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው።

29. በመቅደሱ ግድግዳ ዙሪያ ላይ ሁሉ በውስጥም በውጭም ኪሩቤልን፣ ከዘንባባ ዛፎችና ከፈነዱ አበቦች ጋር ቀረጸ።

30. እንዲሁም የቅድስተ ቅዱሳኑንና የመቅደሱን ወለል በሙሉ በወርቅ ለበጠ።

31. ለቅድስተ ቅዱሳኑም መግቢያ የወይራ ዕንጨት ደጃፎች ሠራ፤ መቃኖቻቸውንና መድረኮቻቸውን ባለ አምስት ማእዘን አደረገ።

32. በሁለቱ የወይራ ዕንጨት መዝጊያዎችም ላይ ኪሩቤልን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈነዱ አበቦችን ቀረጸ፤ በወርቅም ለበጣቸው።

33. እንዲሁም ለዋናው አዳራሽ መግቢያ ባለ አራት ማእዘን የወይራ ዕንጨት መቃን ሠራ፤

34. እያንዳንዳቸው በማጠፊያ የተያያዙ ሁለት ሁለት ሳንቃዎች ያሏቸው ሁለት መዝጊያዎች አበጀ።

35. ኪሩቤልን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችንም ቀረጸባቸው፤ ቅርጹን ሠራ፤ ጥሩ አድርጎም በወርቅ ለበጠው።

36. የውስጠኛውን አደባባይ በሦስት ረድፍ ጥርብ ድንጋይና በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ ሠራው።

37. የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም በአራተኛው ዓመት ዚፍ በተባለው ወር መሠረቱ ተጣለ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 6