ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 6:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በአራት መቶ ሰማንያ ዓመት፣ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ዚፍ በተባለው በሁለተኛው ወር ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ።

2. ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር የሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ሥልሳ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ክንድ፣ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ነበር።

3. በቤተ መቅደሱ ዋነኛ አዳራሽ ፊት ለፊት ያለው በረንዳ ወርዱ እንደ ቤተ መቅደሱ ወርድ ሁሉ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ ወደ ውጭ የወጣ ነበር።

4. ለቤተ መቅደሱም ባለ ዐይነ ርግብ መስኮቶች አበጀ።

5. በዋናው ቤተ መቅደስና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግድግዳ ዙሪያ ልዩ ክፍሎች ያሉት ተቀጥላ ግንብ ሠራ።

6. የምድር ቤቱ ወርድ አምስት ክንድ፣ የመካከለኛው ፎቅ ስድስት ክንድ፣ የሦስተኛው ፎቅ ሰባት ክንድ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ግድግዳ ዘልቆ እንዳይገባም፣ ከቤተ መቅደሱ ግንብ ውጭ ዙሪያውን እርከኖች አደረገ።

7. ቤተ መቅደሱ የተሠራው እዚያው ድንጋዩ ተቈፍሮ ከወጣበት ቦታ በተዘጋጀ ድንጋይ በመሆኑ የመራጃ፣ የመሮ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ በቤተ መቅደሱ አካባቢ አልተሰማም ነበር።

8. የምድር ቤቱ መግቢያ በስተ ደቡብ በኩል ባለው የቤተ መቅደሱ ጐን ሲሆን ወደ መካከለኛውና ከዚያም ወደ መጨረሻው ፎቅ የሚያስወጣ ደረጃ ነበረው።

9. ቤተ መቅደሱንም በዚሁ ሁኔታ ሠርቶ ጨረሰ፤ ለጣራው ተሸካሚ አደረገለት፤ በዝግባ ሳንቃም ከደነው።

10. በቤተ መቅደሱም ዙሪያ በሙሉ፣ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ክፍሎች ሠራ፤ እነዚህንም ከቤተ መቅደሱ ጋር በዝግባ አግዳሚ ዕንጨቶች አያያዛቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 6