ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 5:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የጢሮስ ንጉሥ ኪራም በዘመኑ ሁሉ ለዳዊት ወዳጅ ስለ ነበር፣ ሰሎሞን በአባቱ እግር ለመተካት መቀባቱን በሰማ ጊዜ፣ መልእክተኞቹን ወደ ሰሎሞን ላከ።

2. ሰሎሞንም እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ኪራም መልሶ ላከ፤

3. “አባቴ ዳዊት በዙሪያው ሁሉ ከገጠመው ጦርነት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ መሥራት እንዳልቻለ ታውቃለህ።

4. አሁን ግን አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ሁሉ ሰላም ሰጥቶኛል፤ ጠላትም የለብኝም።

5. እነሆ፣ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአንተ ቀጥሎ በዙፋንህ የማስቀምጠው ልጅህ ነው’ ብሎ እንደ ነገረው፣ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስቤአለሁ።

6. “ስለዚህ የሊባኖስ ዝግባ እንዲቈረጥልኝ ትእዛዝ ስጥ፤ ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋር አብረው ይሠራሉ፤ የሰዎችህንም ደመወዝ አንተ በወሰንኸው እከፍልሃለሁ፤ ከሰዎቼ መካከል እንደ ሲዶናውያን ዕንጨት በመቊረጥ እስከዚህ የሠለጠነ ሰው አለመኖሩን ራስህም ታውቃለህና።”

7. ኪራም የሰሎሞን መልእክት በደረሰው ጊዜ እጅግ ደስ ስላለው፣ “ይህን ታላቅ ሕዝብ እንዲመራ ለዳዊት ጥበበኛ ልጅ ሰጥቶታልና ዛሬ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይግባው” አለ።

8. ስለዚህ ኪራም፣ ለሰሎሞን እንዲህ ሲል ላከበት፤“የላክኸው መልእክት ደርሶኛል፤ የዝግባውንና የጥዱን ግንድ በማቅረብ ረገድ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤

9. ሰዎቼ ግንዱን ከሊባኖስ እስከ ባሕሩ ድረስ ጐትተው ያወርዳሉ፤ እኔም ግንዱ ሁሉ ታስሮ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ በባሕር ተንሳፎ እንዲደርስ አደርጋለሁ፤ እዚያም እኔ እፈታዋለሁ፣ አንተም ትወስደዋለህ፤ አንተም ለቤተ ሰቤ ቀለብ በመስጠት ፍላጎቴን ታሟላለህ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 5