ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 4:23-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ዐሥር ቅልብ ሰንጋዎች፣ ሃያ ግጦሽ መሬት ላይ የሚውሉ በሬዎች፣ መቶ በግና ፍየል እንዲሁም ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ የበረሓ ፍየልና ምርጥ አዕዋፍ።

24. ከወንዙ በስተ ምዕራብ፣ ከቲፍሳ እስከ ጋዛ ያሉትን መንግሥታት ስለ ገዛ፣ በሁሉም አቅጣጫ ሰላም ሆኖለት ነበር።

25. በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር በሰላም ለመኖር በቃ።

26. ሰሎሞን ሠረገላ የሚጐትቱ ፈረሶች የሚያድሩበት አራት ሺህ ጋጣና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት።

27. የየአውራጃው ሹማምትም በየወር ተራቸው ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ማእድ የሚቀርቡትን ሁሉ ምንም ሳያጓድሉ ይቀልቡ ነበር፤

28. እንዲሁም ለሠረገላ ፈረሶችና ለፈጣን ፈረሶች የተመደበውን ገብስና ጭድ ከተፈለገው ቦታ ድረስ ያመጡ ነበር።

29. አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን እንዲሁም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው።

30. የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብፅም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር፤

31. እርሱም ከማንም ሰው ይልቅ ጥበበኛ ነበር፣ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታን፣ ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ደግሞም ከደራል ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አሕዛብ ሁሉ ተሰማ።

32. እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎችን ተናገረ፤ የመሓልዩም ቍጥር ሺህ አምስት ነበር።

33. ከሊባኖስ ዝግባ አንሥቶ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ስለ ዕፀዋት ተናግሮአል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣ ስለ ወፎች፣ በሆዳቸው ስለሚሳቡ እንስሳትና ስለ ዓሦችም ተናግሮአል፤

34. ጥበቡን ከሰሙት ከዓለም ነገሥታት ሁሉ የተላኩ፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለማድመጥ መጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 4