ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 3:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሰሎሞን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አባቴ ዳዊት በእውነት፣ በጽድቅና በቅን ልቦና በፊትህ ስለተመላለሰ፣ ለባሪያህ ታላቅ ቸርነትን አሳይተኸዋል፤ ይህ ታላቅ ቸርነት እንዲቀጥል በማድረግ ዛሬም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተኸዋል።

7. “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ባሪያህ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሃል፤ እኔ ግን ገና ትንሽ ልጅ ስለ ሆንሁ፣ መውጫና መግቢያዬን አላውቅም።

8. ባሪያህ አንተ በመረጥኸው ሕዝብ፣ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር በማይችል ታላቅ ሕዝብ መካከል ይገኛል።

9. ስለዚህ መልካሙንና ክፉውን በመለየት ሕዝብህን ማስተዳደር እንዲችል ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው፤ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊያስተዳድር ይችላል?”

10. ሰሎሞን ይህን በመለመኑ ጌታ ደስ አለው፤

11. ስለዚህ እንዲህ አለው፤ “ለራስህ ረጅም ዕድሜ፣ ብልጽግና እንድታገኝ ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ ሳይሆን፣ በትክክል ማስተዳደር እንድትችል ማስተዋልን ስለ ጠየቅህ፣

12. ይህንኑ አደርግልሃለሁ፤ ከአንተ በፊት ማንም ያልነበረውን፣ ከአንተም በኋላ ማንም የማያገኘውን ጥበብና አስተዋይ ልቡና እሰጥሃለሁ፤

13. ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅኸውን ብልጽግናና ክብር እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም በሕይወት ዘመንህ የሚተካከልህ ማንም ንጉሥ እንዳይኖር ነው።

14. አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድ፣ ሥርዐቴንና ትእዛዜን ብትጠብቅ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ።”

15. ሰሎሞንም ከእንቅልፉ ነቃ፤ እነሆ ሕልም መሆኑን ተረዳ።ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ፣ በጌታ ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብዣ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 3