ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 3:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሰሎሞን የግብፅ ንጉሥ የፈርዖን ወዳጅ ሆነ፤ የፈርዖንንም ልጅ አገባ። እርሱም ቤተ መንግሥቱን፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የኢየሩሳሌምን ዙሪያ ቅጥር ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አስቀመጣት።

2. በዚያን ጊዜ ለእግዚአብሔር ስም ገና ቤተ መቅደስ ስላልተሠራ፣ ሕዝቡ አሁንም መሥዋዕት የሚያቀርበው በማምለኪያ ኰረብታ ላይ ነበር።

3. ሰሎሞን እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፤ በአባቱ በዳዊት ሥርዐትም ይሄድ ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ በኰረብታዎች ላይ መሥዋዕት ይሠዋና ዕጣን ያጥን ነበር።

4. ከሁሉ የሚበልጠው የማምለኪያ ኰረብታ ገባዖን ስለ ነበረ፣ ንጉሡ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። ሰሎሞን በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።

5. በገባዖንም እግዚአብሔር ለሰሎሞን ሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ አምላክም፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ለምን” አለው።

6. ሰሎሞን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አባቴ ዳዊት በእውነት፣ በጽድቅና በቅን ልቦና በፊትህ ስለተመላለሰ፣ ለባሪያህ ታላቅ ቸርነትን አሳይተኸዋል፤ ይህ ታላቅ ቸርነት እንዲቀጥል በማድረግ ዛሬም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተኸዋል።

7. “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ባሪያህ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሃል፤ እኔ ግን ገና ትንሽ ልጅ ስለ ሆንሁ፣ መውጫና መግቢያዬን አላውቅም።

8. ባሪያህ አንተ በመረጥኸው ሕዝብ፣ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር በማይችል ታላቅ ሕዝብ መካከል ይገኛል።

9. ስለዚህ መልካሙንና ክፉውን በመለየት ሕዝብህን ማስተዳደር እንዲችል ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው፤ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊያስተዳድር ይችላል?”

10. ሰሎሞን ይህን በመለመኑ ጌታ ደስ አለው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 3