ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 22:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ከዚያም ሚክያስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በየተራራው ላይ ተበትነው አየሁ፣ እግዚአብሔርም፣ ‘ይህ ሕዝብ ጌታ የለውም፤ እያንዳንዱ በሰላም ወደየቤቱ ይሂድ’ አለ።”

18. የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።

19. ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ስማ፤ ‘እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይ ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ፤

20. እግዚአብሔርም፣ “በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት፣ አክዓብን ማን ያስተው?” አለ።’“ታዲያ አንዱ ይህን፣ ሌላውምያን አለ፤

21. በመጨረሻም፣ ‘አንድ መንፈስ ወጣ፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፣ “እኔ አስተዋለሁ” አለ።’

22. እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።“እርሱም፣ ‘እኔ እወጣለሁ፤ በገዛ ነቢያቱም አፍ ሁሉ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። እግዚአብሔርም፣ “በል እንግዲያው ውጣና አስተው፤ ይሳካልሃል” አለው።

23. “ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ በአንተም ላይ መዓቱን እንደሚያመጣብህ ተናገረ።”

24. ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ በየት በኩል ዐልፎ ነው አንተን መጥቶ ያናገረህ?” ሲል ጠየቀው።

25. ሚክያስም፤ “ይህንማ ለመደበቅ ወደ አንዲት እልፍኝ በሄድህ ዕለት ታውቀዋለህ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 22