ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 22:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በሶርያና በእስራኤል መካከል ለሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም።

2. በሦስተኛው ዓመት ግን የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ ለመጐብኘት ወረደ።

3. የእስራኤልም ንጉሥ ሹማምቱን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ሬማት የእኛ ሆና ሳለች፣ ከሶርያው ንጉሥ እጅ ለመመለስ ምንም እንዳላደረግን አታውቁምን?” አላቸው።

4. ስለዚህ ኢዮሣፍጥን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ሬማት ላይ ለመዝመት አብረኸኝ ለመሄድ ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው።ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ ያው እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፣ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለ።

5. ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው።

6. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ልዝመት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 22