ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 20:28-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. የእግዚአብሔርም ሰው ወጥቶ ለእስራኤል ንጉሥ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እግዚአብሔር የኰረብታ እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ስፍር ቊጥር የሌለው ሰራዊት በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።

29. በየሰፈሩበትም ቦታ ሰባት ቀን ከተፋጠጡ በኋላ በሰባተኛው ቀን ጦርነት ገጠሙ። እስራኤላውያንም በአንዲት ጀምበር ከሶርያውያን ሰራዊት መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ።

30. የቀሩት ወደ አፌቅ ከተማ ሸሹ፤ በዚያም በሃያ ሰባቱ ሺህ ላይ ቅጥሩ ተንዶ ወደቀባቸው። ቤንሀዳድም ወደ ከተማዪቱ ሸሽቶ በመሄድ ወደ አንዲት እልፍኝ ገብቶ ተደበቀ።

31. ሹማምቱም፣ “የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሓሪዎች መሆናቸውን ሰምተናል፤ አሁንም እንነሣና በወገባችን ላይ ማቅ ታጥቀን፣ በራሳችን ላይ ገመድ ጠምጥመን ወደ እስራኤል ንጉሥ እንሂድ፤ ምናልባትም ሕይወትህን ያተርፋት ይሆናል” አሉት።

32. እነርሱም በወገባቸው ላይ ማቅ ታጥቀው፣ በራሳቸው ላይ ገመድ ጠምጥመው ወደ እስራኤል ንጉሥ በመሄድ፣ “አገልጋይህ ቤን ሀዳድ፣ ‘እባክህ በሕይወት እንድኖር ፍቀድልኝ’ ብሎ ይለምንሃል” አሉት።ንጉሡም፣ “እስካሁን በሕይወት አለን? ወንድሜ እኮ ነው” አለ።

33. ሰዎቹም ይህን በደግ በመተርጐም ቃሉን ከአፉ ቀበል አድርገው፤ “አዎን ቤን ሀዳድ ወንድምህ ነው” አሉት።ንጉሡም፣ “በሉ ሂዱና አምጡት” አላቸው፤ ቤንሀዳድም በመጣ ጊዜ፣ አክዓብ ሠረገላው ላይ እንዲወጣ አደረገው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 20