ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 20:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ወደ ከተማዪቱም መልእክተኞች በመላክ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን እንዲህ አለው፤ “ቤን ሀዳድ እንዲህ ይላል፤

3. ‘ብርና ወርቅህ የእኔ ነው፤ የሚያማምሩት ሚስቶችህና ልጆችህም የእኔ ናቸው።’ ”

4. የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ልክ እንዳልኸው ነው እኔም ሆንሁ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” ሲል መለሰለት።

5. መልክተኞቹም እንደ ገና መጥተው እንዲህ አሉት፤ “ቤን ሀዳድ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ብርህንና ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድትሰጠኝ ልኬብህ ነበር፤

6. ሆኖም ነገ በዚሁ ጊዜ ቤተ መንግሥትህንና የሹማምትህን ቤቶች እንዲበረብሩ፣ ሹማምቴን እልካቸዋለሁ። እነርሱም ማናቸውንም ለአንተ ዋጋ ያለውን ሁሉ በእጃቸው በማስገባት ይወስዱታል።’ ”

7. የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው።

8. ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ፣ “የሚልህን አትቀበለው፤ የጠየቀህንም እሺ አትበለው” አሉት።

9. ስለዚህ ለቤን ሀዳድ መልእክተኞች፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ፣ ‘እኔ ባሪያህ በመጀመሪያ ያልኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያሁኑን ጥያቄህን ግን ልፈጽመው አልችልም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህንኑ ይዘው ተመለሱ።

10. ከዚያም ቤን ሀዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ።

11. የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ ‘ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው የጦር ትጥቁን እንደፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው።

12. ቤን ሀዳድ ይህን መልእክት የሰማው አብረውት የነበሩት ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ ነበር፤ ቤን ሀዳድ ሰዎቹን፣ “በሉ ለጦርነት ተዘጋጁ” አላቸው፤ ስለዚህ ከተማዪቱን ለመውጋት ተዘጋጁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 20