ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 20:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ መላ ሰራዊቱን በአንድነት አሰባሰበ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥታት ከነፈረሶቻቸውና ከነሠረገሎቻቸው አብረውት ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከቦ ወጋት።

2. ወደ ከተማዪቱም መልእክተኞች በመላክ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን እንዲህ አለው፤ “ቤን ሀዳድ እንዲህ ይላል፤

3. ‘ብርና ወርቅህ የእኔ ነው፤ የሚያማምሩት ሚስቶችህና ልጆችህም የእኔ ናቸው።’ ”

4. የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ልክ እንዳልኸው ነው እኔም ሆንሁ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” ሲል መለሰለት።

5. መልክተኞቹም እንደ ገና መጥተው እንዲህ አሉት፤ “ቤን ሀዳድ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ብርህንና ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድትሰጠኝ ልኬብህ ነበር፤

6. ሆኖም ነገ በዚሁ ጊዜ ቤተ መንግሥትህንና የሹማምትህን ቤቶች እንዲበረብሩ፣ ሹማምቴን እልካቸዋለሁ። እነርሱም ማናቸውንም ለአንተ ዋጋ ያለውን ሁሉ በእጃቸው በማስገባት ይወስዱታል።’ ”

7. የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው።

8. ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ፣ “የሚልህን አትቀበለው፤ የጠየቀህንም እሺ አትበለው” አሉት።

9. ስለዚህ ለቤን ሀዳድ መልእክተኞች፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ፣ ‘እኔ ባሪያህ በመጀመሪያ ያልኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያሁኑን ጥያቄህን ግን ልፈጽመው አልችልም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህንኑ ይዘው ተመለሱ።

10. ከዚያም ቤን ሀዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ።

11. የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ ‘ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው የጦር ትጥቁን እንደፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው።

12. ቤን ሀዳድ ይህን መልእክት የሰማው አብረውት የነበሩት ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ ነበር፤ ቤን ሀዳድ ሰዎቹን፣ “በሉ ለጦርነት ተዘጋጁ” አላቸው፤ ስለዚህ ከተማዪቱን ለመውጋት ተዘጋጁ።

13. በዚያን ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ብዙ ሰራዊት ታያለህን? ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።

14. አክዓብም፣ “ይህን የሚያደርገው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።ነቢዩም፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን የሚያደርጉት የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖች ናቸው’ ” አለው።“ታዲያ ጦርነቱን የሚጀምረው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።ነቢዩም፣ “አንተው ትጀምራለህ” ብሎ መለሰ።

15. ስለዚህ አክዓብ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑትን ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ወጣት መኰንኖች ጠራ፤ ከዚያም የቀሩትን እስራኤላውያን ሰበሰበ፤ እነዚህም በአጠቃላይ ሰባት ሺህ ነበሩ።

16. እነርሱም ቤን ሀዳድና ከእርሱ ጋር ተባብረው የነበሩት ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሰክረው ሳለ እኩለ ቀን ላይ መጡ።

17. በግንባር ቀደምትነት የወጡት ግን፣ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑት ወጣት መኰንኖች ነበሩ።በዚህ ጊዜ ቤን ሀዳድ ሰላዮች ልኮ ነበርና እነርሱም፣ “ሰዎች ከሰማርያ ወጥተው ወደዚህ በመምጣት ላይ ናቸው” ብለው ነገሩት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 20